Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በተያዘው ዓመት 30 ሺህ ቶን ስንዴ ለማምረት መታቀዱን ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር) ገለጹ

 

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 21፣ 2017 (ኤፍ ቢሲ) በተያዘው በጀት ዓመት በትንሹ 300 ሚሊየን ኩንታል ወይም 30 ሺህ ቶን ስንዴ ለማምረት እቅድ መያዙን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገኙበት 6ኛ ዙር 4ኛ ዓመት 3ኛ መደበኛ ስብስባውን እያካሄደ ነው፡፡

ከፓርላማ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽ እየሰጡ የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ÷ ባለፈው ዓመት ዓመታዊ የGDP እድገት ካቀድነው በላይ 8 ነጥብ 1 በመቶ አሳክተናል ፤ይህም በዓለም ፈጣን እድገት እያመጡ ካሉ ጥቂት ሀገራት ተርታ ኢትዮጵያን የሚያስገባት ነው ብለዋል፡፡

በተያዘው ዓመት 8 ነጥብ 4 በመቶ እድገት ለማምጣት እቅድ መያዙን ያስታወቁት ጠቅላይ ሚኒስተሩ÷ ባለፉት ሶስት ወራት ያየናቸው እንቅስቃሴዎች ከዚያ በላይ ሊመዘገብ እንደሚችል አመላካች መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

ይህ ሲባል ጥቅል እሳቤ ሳይሆን በሴክተር ተከፍሎ መሆኑን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ÷ለአብነት በዓመቱ በግብርናው ዘርፍ 6 ነጥብ 1 በመቶ እድገት ይመዘገባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡

በሰብል ምርት ደግሞ 6 ነጥብ 6 በመቶ እድገት ይመዘገባል ተብሎ ይጠበቃል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በማብራሪያቸው ፡፡

በሌማት ትሩፋት በሚሊየን የሚቆጠሩ ከብቶችን የማዳቀል ሥራ መሰራቱን ጠቁመው÷ በዚህ ዓመት 150 ሚሊየን ጫጩቶች ይዘጋጃሉ፤12 ቢሊየን ሊትር ወተት፤218 ሺህ ቶን ዶሮ ስጋ ፤8 በሊየን እንቁላል ፤12 ነጥብ 28 ሺህ ቶን አሳ ምርት እና 297 ሺህ ቶን ማር ለማግኘት መታቀዱን አንስተዋል፡፡

በዚህም ባለፉት ሶስት ወራት ውጤት ተገኝቶበታል፤ በአጠቃላይም በሌማት ትሩፋት 5 ነጥብ 1 በመቶ እድገት ይጠበቃል ብለዋል፡፡

በዚህ ዓመትም በቡና ወጪ ንግድ ከብራዚል እና ከቬትናም በስተቀር በቡና ልማት ኢትዮጵያን የሚበልጣት ሀገር አይኖርም ብለዋል ፡፡

በሚቀጥሉት ዓመታትም በቡና ጉልደላ እና የችግን ተከላ ስራ ሰርተን ከብራዚል በስተቀር ማንም የማይበልጣት ሀገር እንዳይኖር እየተሰራ ነው፤ባለፈው ዓመት በቡና የወጪ ንግድ 1ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር ገቢ አግኝተናል ፣በዚህ ዓመት 2 ቢሊየን ዶላር ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡

በዚህም 450 እስከ 500 ሺህ ቶን ቡና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ መታቀዱን አንስተው÷ በሻይ ዘርፍም በዚህ ዓመት 20 የሻይ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎችን ለመክፈት መታቀዱንና በሚገባ ከተሰራ በሻይ ምርትም ከአምራች ሀገራት ተርታ ለመግባት ያለን እድል ሰፊ ነው ብለዋል፡፡

ስንዴን በሚመለከት ደግሞ ዘንድሮ ከ 8 ነጥብ 2 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት በስንዴ እንደሚሸፈንና ከዚህም በትንሹ 300 ሚሊየን ኩንታል (30 ሺህ ቶን )ስንዴ ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልፀዋል፡፡

ይህን ለማሳካት በቂ ገበያ እና የእሴት መጨመር ስራ ከሰራን ምርት ለማሳደግ ያለን አቅም እየሰፋ ይሄዳል ነው ያሉት፡፡

በሌላ በኩል ሰሊጥ ፣ ለውዝ ፣ አኩሪ አተርና ቦሎቄ በስፋት ማምረት መቻሉንና ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል፡፡

በፌቨን ቢሻው

Exit mobile version