የሀገር ውስጥ ዜና

ከዚህ ዓመት ጀምሮ ሀገራዊ ማንሠራራት የምንጀምርበት ነው – ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር)

By Feven Bishaw

October 31, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 21፣ 2017 (ኤፍ ቢሲ) ከዚህ ዓመት ጀምሮ ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ማንሠራራት የምንጀምርበት ዓመት ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለፁ፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገኙበት 6ኛ ዙር 4ኛ ዓመት 3ኛ መደበኛ ስብስባውን እያካሄደ ነው፡፡

ከፓርላማ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽ እየሰጡ የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)÷ ከዚህ ዓመት ጀምሮ ለኢትዮጵያ እንደ ሀገር ማንሠራራት የምንጀምርበት ዓመት ነው ብለዋል፡፡

ይህ ዓመት ሪፎርሞቻችንን ጨርሰን ሀገራዊ ማንሠራራት የምንጀምርበት እና በታሪካችን ዐይተን የማናውቃቸው ውጤቶችን እያየን ለትውልድ የማፅናት ሥራ የምናሸጋግርበት ዘመን መጀመሪያ ነው ሲሉም ገልዋል፡፡

ለሥድስት ዓመት በሪፎርሙ ዓመታት የተለያዩ ተቋማትን የማፍታታት ሥራ ስንሠራ ቆይተናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ በመጨረሻ ይዞን የቆው የኢኮኖሚ ሪፎርም ነበር፤ እሱም በቅርቡ በተሟላ መልኩ ጀምሯል ብለዋል፡፡

በዚህም ከዚህ ዓመት ጀምሮ የማንሠራራት ዓመት ይሆንልናል፤ በዚህ የማንሠራራት ዓመት ውስጥም በርካታ ውጤቶች ይጠበቃሉ፤ የሚቀጥልለው ደረጃም ማፅናት ይሆናል ሲሉ አብራርተዋል፡፡

የማትናጹን ስራ ደግሞ ትውልድ የሚያስቀጥለው ይሆናል ነው ያሉት፡፡

የማንሠራራት ዓመት ይሆናል ስንል እንዲሁ ምኞት ሳይሆን ባለፉት ዓመታት በታየው መልክ መንግሥት የማይነጥፍ ሐሳብ ይዞ ይነሳል፤ ሐሳቦቹንም በተግባር የሚዳሰስ ለማድረግ ይተጋል በማት አስረድተዋል፡፡

ከትጋት በኋላ የሚጠበቅ ውጤት በበቂ ደረጃ ካልመጣም ሊያዘናጋ ይችላልና በእኛ ሁኔታ ግን አመርቂ ውጤቶች እያገኘን እንሄዳለን ሲሉ በአፅንኦት ገልጸዋል፡፡

 

በፌቨን ቢሻው