Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የመገናኛ ቦሌ የኮሪደር ልማት የስማርት ቴክኖሎጂ ውጤቶች በሥራ ላይ የዋለበት መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 20፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የመገናኛ ቦሌ የኮሪደር ልማት የመጀመሪያው ምዕራፍ የስማርት ቴክኖሎጂ ውጤቶችን በሥራ ላይ የዋለበት መሆኑን በአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር በምክትል ከንቲባ ማዕረግ ዋና ሥራ አስኪያጅ ጥራቱ በየነ ገለጹ፡፡

መሥመሩ ዲጂታል ፖሎች፣ የመኪና ቻርጅ ማድረጊያ እና ሌሎች ዘመናዊ ስማርት ግብዓቶችን ያካተተ መሆኑን አቶ ጥራቱ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት ገለጻ ላይ አብራርተዋል፡፡

የኮሪደር ልማቱ 4 ነጥብ 3 ኪሎ ሜትር እንደሚሸፍን አንስተው÷ ከዚህ ቀደም የተለያዩ ተግዳሮቶች ያሉበት እና ለእንቅስቃሴ የማይመች እንደነበር አስረድተዋል፡፡

ለአብነትም የእግረኛ እና የብስክሌት መንገድ እንዳልነበረው ጠቅሰዋል፡፡

መሥመሩ በቦሌ በኩል የሚገቡ ዓለም አቀፍ የእንግዶች መቀበያ መንገድ በመሆኑ÷ በአሁኑ ሠዓት አብዛኛው ሥራዎቹ በመጠናቀቅ ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

ይህ መሥመር ከዚህ ቀደም የነበረውን በማፍረስ እንደገና ተስፋፍቶ መሠራቱን እና የመንገድ ሥራውም ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቋል ነው ያሉት።

የአስፓልቱ ስፋት 68 ሜትር መሆኑን በመግለጽ ለትራፊክ ክፍት መደረጉንም አስታውቀዋል፡፡

በዚህ የኮሪደር ልማት ሥራ ካፌ፣ ሱቆች፣ መፀዳጃ ቤቶች፣ የመኪና ማቆሚያ፣ የኤሌክትሪክ መኪኖች ቻርጅ ማድረጊያና ሌሎች ተጨማሪ የማኅበረሰብ አቀፍ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ የመሠረተ-ልማቶች በሥራ ላይ ውለዋል ብለዋል።

በሌላ በኩል መገናኛ የሚገኘው የውስጥ ለውስጥ የእግረኛ መንገድ በ45 ቀናት ውስጥ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት እንደሚደረግ አመላክተዋል፡፡

በታሪኩ ወ/ሰንበት

Exit mobile version