Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

መገናኛ ብዙኃን ሀገራዊ አንድነትን የሚያጠናክር ዘገባ መሥራት ይጠበቅባቸዋል- ለገሠ ቱሉ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 20፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) መገናኛ ብዙኃን ሀገራዊ አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ ትክክለኛ እና ሚዛናዊ ዘገባዎች መሥራት እንዳላባቸው የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሠ ቱሉ (ዶ/ር) አስገነዘቡ።

“ሚዲያ ለብሔራዊ ትርክትና ሀገር ግንባታ” በሚል መሪ ሐሳብ ለመገናኛ ብዙኃን አመራሮችና ባለሙያዎች ለሦስት ቀናት ሥልጠና ተሰጥቷል።

በሥልጠናው የትርክት እመርታ ከታሪካዊ ስብራት ወደ ሀገራዊ ምልዐት፤ እመርታ ከሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ወደ ብልጽግና እና የፖለቲካ እመርታ ከዴሞክራሲ መብት ወደ ሀገራዊ ኃላፊነት በሚሉ ርዕሶች ላይ   የስልጠና ሠነዶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

የፖለቲካ እመርታ ከዴሞክራሲ መብት ወደ ሀገራዊ ኃላፊነት በሚል ርዕስ ሠነድ ያቀረቡት ለገሠ ቱሉ (ዶ/ር)÷ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ለሀገረ መንግሥት ግንባታ መሠረት የሚጥሉ በርካታ የሪፎርም ሥራዎች መከናወናቸውን አብራርተዋል፡፡

በዚህም ሕዝብን ተጠቃሚ ያደረጉ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊእና ፖለቲካዊ ስኬቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።

ከዚህ አኳያ ሀገራዊ የሪፎርም ሥራዎችን ውጤታማ ለማድረግ መገናኛ ብዙኃን የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ማስገንዘባቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በቀጣይም ስለ ሪፎርሙ መነሻዎች፣ ሂደቶች፣ ስኬቶች፣ ተግዳሮቶችና ቀጣይ አቅጣጫዎችን ሕዝቡ በሚገባ እንዲገነዘብ ማድረግ ላይ በትኩረት ሊሠሩ ይገባል ነው ያሉት፡፡

ለሪፎርሙ ስኬት የሕዝብ ተሳትፎ እንዲጎለበት አስተማሪ ሥራዎች መጠናከር እንዳለባቸውም አንስተዋል፡፡

የተሳሳቱ መረጃዎችን የማጥራት እና የፅንፈኝነት አስተሳሰብን መከላከልና መቅረፍ ላይ መሥራት እንዳለባቸውም አስረድተዋል፡፡

ሀገራዊ አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ ትክክለኛና ሚዛናዊ ዘገባዎች መሥራት እንዳላባቸውም ነው ሚኒስትሩ ያስገነዘቡት፡፡

Exit mobile version