የሀገር ውስጥ ዜና

ሰብዓዊ ድጋፍን ላልተገባ ዓላማ ያዋሉ አካላትን ተጠያቂነት ለማስፈን እየተሠራ ነው- ሚኒስቴሩ

By ዮሐንስ ደርበው

October 30, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 20፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ለሰብዓዊ ድጋፍ የተዘጋጀ ዕርዳታን ላልተገባ ጥቅም ያዋሉ አካላትን ተጠያቂነት ለማረጋገጥ እየተሠራ መሆኑን ፍትሕ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የፍትሕ ሚኒስትር ዴዔታ ተስፋዬ ዳባ ከአሜሪካ ዓለም አቀፍ ተራድዖ ድርጅት (ዩ ኤስ ኤይድ) የኢትዮጵያ ተልዕኮ ምክትል ዳይሬክተር ቲም ስቴይን ጋር ተወያይተዋል፡፡

በዚሁ ወቅት ሚኒስትር ዴዔታው የሰብዓዊ ድጋፍ በሀገሪቱ በሁሉም ክልሎች ፍላጎቱ ባለበት አካባቢ ሲከፋፈል እንደነበር አስረድተዋል፡፡

እንዲሁም በአንድ አንድ ቦታዎች የሰብዓዊ ድጋፉን አቅጣጫ በማስቀየር በነጋዴዎች እጅ ገብቶ በገበያ ላይ መገኘቱን ጠቅሰዋል፡፡

ይህን ተግባር በፈፀሙ ግለሰቦችና የተቋም አመራሮች ላይ የወንጀል ምርመራ የሚያከናውን ቡድን በማዋቀር ወደ ሥራ ተገብቷል ማለታቸውን የፍትሕ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡

ምርመራውም በቅርቡ እንደሚጠናቀቅ እና ያልተገባ ድርጊት የፈፀሙ ግለሰቦችንና አካላትን ተጠያቂ ለማድረግ እየተሠራ እንደሚገኝ አረጋግጠዋል፡፡

ቲም ስቴይን በበኩላቸው ዩ ኤስ ኤይድ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመተባበር በሀገሪቱ ሰብዓዊ ድጋፍ ለሚፈልጉ ዜጎች ተገቢው ዕርዳታ እንዲደርሳቸው ጥረት እያደረገ ነው ብለዋል፡፡

በሂደቱ የሰብዓዊ ድጋፍ አቅጣጫ ባስቀየሩ ግለሰቦች ላይ ተገቢው ተጠያቂነት ሊረጋገጥ እንደሚገባ አንስተው÷ ይህንን ለማድረግ አስፈላጊውን መረጃ በመስጠት ከሚኒስቴሩ ጋር በትብብር እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡