የሀገር ውስጥ ዜና

በአቶ አሕመድ ሺዴ የተመራ ልዑክ ከዩሮ ቦንድ አበዳሪ ሀገራት ጋር ተወያየ

By ዮሐንስ ደርበው

October 30, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 20፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ የተመራ ልዑክ በዋሽንግተን እየተካሄደ ከሚገኘው የዓለም ባንክ እና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይ ኤምኤፍ) ዓመታዊ ስብሰባ ጎን ለጎን ከዩሮ ቦንድ አበዳሪ ሀገራት ጋር ተወያይቷል፡፡

ውይይቱ በቡድን 20 አባል ሀገራት የጋራ መርሐ-ግብር መሰረት የኢትዮጵያ የዕዳ አያያዝ መሻሻል ላይ ትኩረት ማድረጉ ተገልጿል፡፡

በዚሁ ወቅት አቶ አሕመድ ሺዴ ኢትዮጵያ ልዑክ በመንግሥት በኩል ስለተካሄዱ የኢኮኖሚ ሪፎርሞች አብራርተዋል፡፡

በተለይም መንግሥት የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባትን ለማስተካከል እና አካታች የሆነ እድገትን በሀገሪቱ  እውን ለማድረግ በማሰብ የኢኮኖሚ ሪፎርም ማካሄዱን በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ ያስገባ የብድር አያያዝን ተግባራዊ ለማድረግ እንዲሁም በተገቢው ጊዜ እና ሁኔታ ብድርን ለመመለስ በሚያስችሉ  መንገዶች ላይ በጋራ እንደሚሠሩም ተገልጿል፡፡