Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ሙስናን የሚጸየፍ ትውልድ ለማፍራት በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 20፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ለሀገር አቀፍ የሥነ-ምግባርና የሙስና መከላከል ረቂቅ ፖሊሲ የግብዓት ማሰባሰብ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የፌዴራል ሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን አስታውቋል፡፡

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ሳሙኤል ኡርቃቶ (ዶ/ር) እንደገለጹት÷ ረቂቅ ፖሊሲው በጥናት ላይ የተመሠረተና የሀገራትን የአሠራር ተሞክሮ ከግምት ያስገባ ነው።

በረቂቅ ፖሊሲው ላይም ኢትዮጵያ ተቀብላ ያጸደቀቻቸውን ቀጣናዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የሙስና መከላከል ሥምምነቶች በተሟላ መንገድ ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

ረቂቅ ፖሊሲው ጸድቆ በሥራ ላይ ሲውል ባለድርሻ አካላት የሙስና ወንጀሎችን ለመከላከል በሚያደርጉት ጥረት ቅንጅታዊ አሠራርን ለማጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንዳለው ገልፀዋል።

በተለይም ሙስናን የሚጸየፍ ትውልድ ለማፍራት ረቂቅ ፖሊሲው ትኩረት ማድረጉን ነው አጽንኦት የሰጡት፡፡

የሙስና ወንጀሎችን ቀድሞ ለመከላከል ከሚደረገው ጥረት ባሻገር ሕብረተሰቡን በማሳተፍ ተጠያቂነትና ሕግ የማስከበር ሥራ በረቀቂ ፖሊሲው ላይ ትኩረት እንደተሰጠው አንስተዋል።

ረቂቅ ፖሊሲው የመንግሥት ተቋማትን የአፈጻጸም ብቃት ሊያሳድጉ የሚችሉ የግልጸኝነትና የተጠያቂነት መርህን ተግባራዊ እንዲያደርጉ የሚያግዝ መሆኑንም ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡

የትውልድ ሥነ-ምግባር ግንባታ፣ የተቋማት ግልጽ አሠራር፣ የሙስና ወንጀል ተጠያቂነትና ሕግ ማስከበር የባለድርሻ አካላትን ትብብር ማጠናከርም ሌላኛው የረቂቅ ፖሊሲው የትኩረት መስክ መሆኑን አብራርተዋል።

Exit mobile version