Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በትግራይ ክልል የወባ በሽታ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ እየተሠራ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 20፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በትግራይ ክልል የወባ በሽታ በሰው ሕይወት ላይ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ በየደረጃው ከሚገኙ አካላት ጋር በትብብር እየተሠራ መሆኑን የክልሉ ጊዜያዊ አሥተዳደር ጤና ቢሮ አስታወቀ፡፡

በክልሉ የሕብረተሰቡን ጤና በዘላቂነት ለማስጠበቅ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የቢሮው ኃላፊ ዶክተር አማኑኤል ኃይለ ተናግረዋል፡፡

የግብዓት አቅርቦትና የሕክምና መስጫ ተቋማት ተደራሽነትን በማስፋት ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን የመከላከል ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

እንዲሁም በህመም ለተጠቁ ዜጎች ተገቢው የሕክምና አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡

የጤና ባለሙያዎችን በመመደብ፣ ወባ የሚከሰትባቸው አካባቢዎችን በመለየት፣ የቅድመ መከላከል ሥራና ለወባ መራቢያ ምቹ የሆነ የታቆረ ውኃን የማፋሰስ ተግባር መከናወኑንም ጠቅሰዋል፡፡

የሕብረተሰቡን ግንዛቤ የማሳደግና የሕክምና አገልግሎቱን በስፋት ተደራሽ የማድረግ ሥራም እየተከናወነ መሆኑን ነው ያስረዱት፡፡

በክልሉ በርካታ ሰዎች በወባ በሽታ መያዛቸውን በመጥቀስ÷ በሽታው በሰው ሕይወት ላይ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ በየደረጃው ከሚገኙ አካላት ጋር በትብብር እየተሠራ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

Exit mobile version