አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 20፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የምግብ ሥርዓት እና ሥርዓተ-ምግብ ተግባራትን ከገጠር ልማት ኮሪደር ጋር በማስተሳሰር መምራት እንደሚገባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር) ገለጹ፡፡
በክልሉ የምግብ ሥርዓት እና ሥርዓተ-ምግብ መዋቅራዊ አደረጃጀት ለመፍጠር የሚያስችል የንቅናቄ መድረክ በቦንጋ ከተማ ተካሂዷል፡፡
ርዕሰ መሥተዳድሩ በዚሁ ወቅት በምግብ ሥርዓት እና ሥርዓተ-ምግብ የተከናወኑ ተግባራት በተሻለ ደረጃ መሻሻሎች የታዩበት መሆኑን ተናግረዋል።
በክልሉ የምግብ ሥርዓት እና ሥርዓተ-ምግብ ማስተባበሪያ በማቋቋምና የአማካሪ ካውንስል በማደራጀት ተጨባጭ ለውጦች መኖራቸውንም ጠቅሰዋል፡፡
ፕሮግራሙ መቀንጨርንና ሞትን መቀነስ ብሎም በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ተልዕኮ ያለው ስለሆነ÷ ከገጠር ኮሪደር ልማት ጋር በማስተሳሰር መምራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በክልሉ በተከናወኑ ተግባራት ለውጦች ይኑሩ እንጂ እየተስተዋለ የሚታየው የመረጃ ጥራት ክፍተት በትኩረት ሊቀረፍ እንደሚገባም አስረድተዋል፡፡
በመድረኩ የብዝኃ ሴክተር የምግብና ሥርዓተ -ምግብ ፕሮግራም የ2016 በጀት ዓመት አፈጻጸም ፣ የፕሮግራሙ መዋቅራዊ አደረጃጀት ለመፍጠር የተዘጋጀ ሠነድና በማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤቱ የተከናወኑ ሥራዎች ቀርበው ውይይት መደረጉን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ አመላክቷል፡፡