የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ ወደ ዲጂታል ሕዝብና ቤት ቆጠራ እየተጓዘች ነው – አቶ ተመስገን ጥሩነህ

By ዮሐንስ ደርበው

October 30, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 20፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ሰው ሠራሽ አስተውሎትን በመጠቀም ኢትዮጵያ ወደ ሙሉ የዲጂታል ሕዝብና ቤት ቆጠራ እየተጓዘች ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡

9ኛው የአፍሪካ ስታትስቲክስ ኮሚሽን “አፍሪካዊ ፈጠራን በስታቲስቲክስ ልማት ውስጥ ማስፈን” በሚል መሪ ሐሳብ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

ለሦስት ቀናት በባለሙያዎች ደረጃ ሲካሄድ የነበረው ጉባዔ ዛሬ ከፍተኛ መሪዎችና የዓለም አቀፍ ተቋማት ባለሙያዎች በተገኙበት ነው እየተካሄደ የሚገኘው፡፡

አቶ ተመስገን በዚሁ ወቅት በተደራጀ መረጃና ሰው ሠራሽ አስተውሎትን በመጠቀም እንዲሁም የስታትስቲክስ ትክክለኛነትን በማሻሻሻል ኢትዮጵያ ወደ ሙሉ የዲጂታል ሕዝብና ቤት ቆጠራ እየተጓዘች መሆኗን ተናግረዋል፡፡

የአፍሪካ የነገ እጣ ፈንታ ዛሬ በምናቅደው፣ በምንፈጥረው ሥራ እና አቅም ላይ የተመሰረተ ነውም ብለዋል፡፡

በመተባበር ችግሮቻችንን ወደ እድል መቀየር እንችላለን ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ልማትን የሚደግፍ፣ ተጠቃሚነትን የሚያበረታታ እና ግቦቻችንን ለማሳካት የሚረዳን የስታትስቲክስ ሥርዓት መገንባት እንችላለን ብለዋል።

በጉባዔው የተለያዩ ሀገራት የተሻሉ የስታትስቲክስ ልምዶች የተዳሰሱበት ሲሆን÷ በአፍሪካ ስታትስቲክስ ዕድሎችና ተግዳሮቶች ላይ ያተኮሩ መረጃዎችም ቀርበዋል።

የአፍሪካ ስታትስቲክስ አሠራር በቴክኖሎጅ የተደገፈና የተደራጀ አቅም ሊፈጥር እንደሚገባውም በመድረኩ ተነስቷል፡፡

ለዘርፉ የቀጣይ የተደራጀ ሥራ አስፈላጊው የቴክኖሎጂና የፋይናንስ ሃብቶች ከተለያዩ ምንጮችና ዓለም አቀፍ የዘርፉ ተቋማት ትብብር እንዲደረግ ተጠይቋል።

በፍሬሕይዎት ሰፊው