አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 20፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባን የበለጸገ ታሪክ የሚያከብር የቱሪዝም አቅርቦት ለማዳበር በሁሉም ባለድርሻ አካላት መካከል የተቀናጀ ጥረት ወሳኝ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስገነዘቡ፡፡
አዲስ አበባ በርካታ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁነቶችን በማስተናገድ የቆየች ከተማ መሆኗን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ገልጸዋል፡፡
መዲናዋ ቀዳሚ መዳረሻ የመሆን ግዙፉ ዐቅሟ ከጊዜ ወደ ጊዜ እውን እየሆነ መምጣቱንም አስታውቀዋል፡፡
አዲስ አበባ ለነዋሪዎች ምቹ ከተማ ለመሆን በምታደርገው ጉዞ ብቻ ሳይሆን በእንግዳ ተቀባይነቷም የላቀች እንድትሆን የባለድርሻ አካላት ቅንጅት ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
እንዲሁም ከፍተኛ ጥራት ያለው የአገልግሎት አሰጣጥን፣ ደኅንነትን እና የመዲናችንን የበለጸገ ታሪክ የሚያከብር የቱሪዝም አቅርቦትን ለማዳበር በሁሉም ባለድርሻ አካላት መካከል የተቀናጀ ጥረት ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡