ጤና

በአማራ ክልል በ80 ወረዳዎች የወባ በሽታ ሥርጭት ተከሰተ

By Shambel Mihret

October 30, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 20፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል በ80 ወረዳዎች የወባ በሽታ ሥርጭት መከሰቱን የክልሉ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡

በተለይም በጎጃም፣ ጎንደር፣ ዋግኸምራ፣ ሰሜን ወሎ እና አካባቢዎቻቸው የሚገኙ ከ80 በላይ ወረዳዎች ውስጥ የወባ በሽታ ሥርጭት መስፋፋቱን ነው የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ የተናገሩት፡፡

በአካባቢዎቹ በየሣምንቱ ከ70 ሺህ በላይ የወባ ታማሚዎች ሪፖርት እየደረሳቸው መሆኑን ለለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የገለጹት አቶ በላይ÷ ከ80ዎቹ መካከል በ40 ወረዳዎች በከፍተኛ ሁኔታ በሽታው መሠራጨቱን አረጋግጠዋል፡፡

የክልሉ መንግሥትም ችግሩን ለመከላከል እንዲቻል ጤና ጣቢያ መር የማኅበረሰብ አቀፍ የወባ መከላከል ዘመቻ ማስጀመሩን አመላክተዋል፡፡

ንቅናቄው እስከ ታኅሣስ 30 በትኩረት እንደሚከናወን ጠቁመው÷ ዘወትር ዓርብ ማኅበረሰቡን ያሳተፈ የአካባቢ ቁጥጥር እንደሚደረግ አስገንዝበዋል፡፡

በዚህ ተግባር ማኅበረሰቡ በንቃት እንዲሳትፍም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በሰለሞን ይታየው