አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 20፣ 2017(ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ እና ጀርመን መንግሥት ለተለያዩ ፕሮጄክቶች ማስፈፀሚያ የሚውል የ30 ሚሊየን ዩሮ የድጋፍ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡
ስምምነቱን የተፈራረሙት የገንዘብ ሚኒስትር ዴዔታ ሰመሪታ ሰዋሰው እና የጀርመኑ ኬ ኤ ፍ ደብሊው ልማት ባንክ የፋይናንስ ኦፊሰር ቤርነድ ሎዊን ናቸው፡፡
በስምምነቱ መሠረት የጀርመን መንግሥት በጀርመኑ ኬ ኤፍ ደብሊው ባንክ በኩል በሁለት ዋና ዋና ፕሮጄከቶች ላይ ለኢትዮጵያ የፋይናንስ ድጋፍ እንደሚያደርግ ተገልጿል፡፡
በዚሁ መሠረት ድጋፉ በኢትዮጵያ ግብርናን በማዘመን ምርታማነትን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት የግብርና ማሽነሪዎች ወደ ሀገር ቤት እንዲገቡ እገዛ ለማድረግ የሚውል መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡
ይህም አርሶ አደሮች በዘመናዊ የግብርና ማሽነሪዎች በመታገዝ ምርትና ምርታማነታቸውን እንዲያሳድጉ እና የገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ያስችላል ተብሏል፡፡
በተጨማሪም ድጋፉ በኢትጵያ የግሉን ዘርፍ ለማበረታታት የሚውል ሲሆን÷ በዚህም ለጥቃቅን፣ አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የሚደረገውን የፋይናንስ አቅርቦት የሚያሻሻል መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
ይህ የፋይናንስ ድጋፍም በጥቃቅን አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የተሰማሩ ሴቶች እና ወጣቶችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ነው የተመለከተው፡፡