የሀገር ውስጥ ዜና

አቶ አህመድ ሺዴ ከእንግሊዝ የልማት ሚኒስትር እና ከጀርመን የኢኮኖሚ ትብብር እና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ጋር ተወያዩ

By amele Demisew

October 29, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 19፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ ከእንግሊዝ የልማት ሚኒስትር እና ከጀርመን የኢኮኖሚ ትብብር እና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ከተመራ ልዑክ ጋር የሁለትዮሽ ውይይት አድርገዋል፡፡

ከአለም ባንክና ከአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም አመታዊ ስብሰባ ጎን ለጎን በተደረገው ውይይት ሚኒስትሩ ከእንግሊዙ የልማት ሚኒስትር አኔሊሴ ዶድስ ጋር በኢትዮጵያ ወቅታዊ፣ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ ውጤታማ ውይይት ማድረጋቸው ተገልጿል፡፡

በቅርቡ በኢትዮጵያ ስለ ተተገበረው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ለሚኒስትሩ ገለጻ ያደረጉት አቶ አህመድ ለፕሮግራሙ ተፈጻሚነትም የእንግሊዝ መንግስት ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል ፡፡

በተመሳሳይ አቶ አህመድ ሺዴ ከጀርመን የኢኮኖሚ ትብብር እና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ኒልስ አነን ከተመራ ልዑክ ጋር የተወያዩ ሲሆን÷ በውይይታቸውም ኢትዮጵያ እና ጀርመን ያላቸውን የልማት አጋርነት ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል፡፡

ኢትዮጵያ በቅርቡ መተግበር የጀመረቻቸው የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች፣ በቀጣናው የኢኮኖሚ ትስስር እና መረጋጋት ላይ ያላት ሚና፣ የሀገራቱ የልማት የትኩረት አቅጣጫዎች እና የጀርመን የግሉ ዘርፍ በኢትዮጵያ የሚያደርገውን ኢንቨስትመንት ማሳደግ በሚሉት ላይም ሰፊ ውይይት ማድረጋቸው ተገልጿል፡፡

ሁለቱ ወገኖች ጀርመን በሁለትዮሽ የድጋፍ ማዕቀፏ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች እና የሪፎርም ስራዎችን መደገፍ በምትችልበት ሁኔታ ላይ ሀሳብ መለዋወጣቸውን ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በተመሳሳይ አቶ አሕመድ ሽዴ ከዓለም ባንክ የኦፕሬሽን ማኔጂንግ ዳይሬክተር አና ቤርዴ ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይቱ አና ቤርዴ ÷ባንኩ ኢትዮጵያ ሁሉንም ዜጎቿን ተጠቃሚ ማድረግን አላማ ላደረገው ሁሉን አካታች የኢኮኖሚ ማገገሚያ እና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የኢነርጂ አቅርቦት ተደራሽነትን ለማሳደግ የያዘችውን ግብ እና በሰው ኃይል ልማት እየተገበረች ያለውን ብሔራዊ መርሃ ግብር ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን ገልፀዋል።

ባንኩ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ፣ ለግሉ ዘርፍ ያለውን ምቹ የኢንቨስትመንት ምህዳር ታሳቢ ባደረገ መልኩ ለዘርፉ ልማት ድጋፍ እንደሚያደርግም አመልክተዋል።