Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

አሊባባ ግሎባል ኢኒሼቲቭ አካዳሚውን በኢትዮጵያ ሊከፍት ነው

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 19፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) አሊባባ ግሎባል ኢንሼቲቭ በኤሌክትሮኒክ ንግድ(E- commerce) ስልጠና መስጠት የሚያስችለውን ግሎባል አካዳሚ በኢትዮጵያ ሊከፍት መሆኑን አስታውቋል።

ኢኒሼቲቩ ከዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ኢትዮጵያ ማህበር ጋር በመተባበር በኤሌክትሮኒክ ንግድ ዘርፍ ከተሰማሩ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ጋር በአዲስ አበባ ተወያይቷል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ይሽሩን አለማየሁ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት÷ መንግስት ዲጂታል ምጣኔ ሃብትን እውን ለማድረግ በፖሊሲ፣ በዲጂታል ክህሎትና በመሰረተ ልማት ዘርፈ ብዙ ተግባራትን ማከናወኑን ገልጸዋል።

በዲጂታል ምጣኔ ሃብት ሽግግር ወጣቱን የስራ እድል ተጠቃሚ ለማድረግ አሊባባን ጨምሮ ከአለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር የሚደረግ ትብብር ትልቅ ፋይዳ እንዳለውም አንስተዋል።

ኢትዮጵያውያን ወጣቶችም ከአሊባባና ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት የሚወስዷቸውን ልምዶች ወደ ተግባር በመቀየር ዲጂታል ምጣኔ ሃብትን እውን ለማድረግ የበኩላቸውን እንዲወጡ አስገንዝበዋል።

የአሊባባ ግሎባል ኢኒሼቲቭ ከፍተኛ አማካሪ ዳን ሊዩ በበኩላቸው÷ ኢኒሸቲቩ በኢትዮጵያ ግሎባል አካዳሚውን በመክፈት በአፍሪካ በርካታ ስራ ፈጣሪዎችን ለማፍራት ማቀዱን ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ ከአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር የሚጣጣሙ መርሃ ግብሮች ላይ ትኩረት በማድረግ በኤሌክትሮኒክ ግብይት ክህሎትን ለማዳበር እንደሚሰራም ገልጸዋል።

ኢኒሼቲቩ በቻይናው አሊባባ ዓለም አቀፍ የዲጂታል ንግድ ቡድን የዓለም የኤሌክትሮኒክ ንግድ አካል ሲሆን ሙያዊ ስልጠና በመስጠት ላይ ትኩረቱን ያደረገ ኢኒሼቲቭ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

Exit mobile version