ዓለምአቀፋዊ ዜና

በሰሜን ጋዛ 4 የእስራኤል ወታደሮች ተገደሉ

By Feven Bishaw

October 29, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 19፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) እስራኤል በሰሜን ጋዛ የምትፈጽመው የአየር ጥቃት ተጠናክሮ መቀጠሉ ተገልጿል፡፡

የጋዛ ጤና ሚኒስቴር እንዳስታወቀው÷የእስራኤል ጦር በሰሜን ጋዛ በተለያዩ አካባቢዎች በፈጸመው የአየር ጥቃት በርካታ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳቶች ደርሰዋል፡፡

እስካሁን ድረስም በአየር ጥቃቱ ሕይወታቸው ያለፉት ዜጎች ቁጥር 109 መድረሱን ነው ሚኒስቴሩ የገለጸው፡፡

የእስራኤል ጦር በበኩሉ÷በሰሜን ጋዛ የሚንቀሳቀሰው የሃማስ ታጣቂ ቡድን ላይ የተጠናከረ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን አመልክቷል፡፡

ይሁን እንጂ በተካሄደው ጦርነት የደረሰውን ጉዳት ከመግለጽ መቆጠቡ ተጠቁሟል፡፡

በሌላ በኩል በሰሜን ጋዛ እየተካሄደ በሚገኘው ጦርነት አራት የእስራኤል ወታደሮች መገደላቸውን የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት አስታውቋል፡፡

ከተገደሉት ወታደሮች በተጨማሪ አንድ የእስራኤል ኦፊሰር ከባድ ጉዳት እንደደረሰበት አልጀዚራ በዘገባው አስፍሯል፡፡

ወታደሮቹ በአካባቢው ከባድ ውጊያ ሲያደርጉ እንደነበር የተገለጸ ሲሆን÷ የሟቾቹ ማንነት ለቤተሰቦቻቸው ይፋ መደረጉም ተመላክቷል፡፡