Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የትምህርት ሥርዓቱን የምናሻሽለው ኢትዮጵያን ከድህነት የሚያወጣ ትውልድ ለመፍጠር ነው- ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 19፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የትምህርት ሥርዓቱን የምናሻሽለው ሀገሪቱን ከድህነት የሚያወጣና ኢኮኖሚውን የሚሸከም ትውልድ ለመፍጠር ነው ሲሉ የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ገለጹ፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር አመራሮችና ሰራተኞች የሚኒስቴሩን የበጀት ዓመቱን የመጀመሪያ ሩብ አመት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ተወያይተዋል፡፡

በውይይቱ ብርሃኑ ነጋ(ፕ/ር)÷በትምህርት ሥርዓቱ ሪፎርም ማካሄድ ያስፈለገው ሀገሪቱን ከድህነት የሚያወጣና ኢኮኖሚውን የሚሸከም ትውልድ ለመፍጠር ነው ብለዋል፡፡

ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለች ሀገር ለማስረከብ መስዋዕትነት መክፈል እንደሚገባ የገለፁት ሚኒስትሩ በተለያዩ ዘርፎች እየተካሄዱ ላሉ ሀገራዊ የለውጥ ርምጃዎችም ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባ አንስተዋል።

በዚህ ዘመን ከዓለም ጋር እኩል መራመድ አለመቻላችን እንደ ዜጋ ቁጭት ሊሰማንና ለለውጥ መትጋት ይኖርብናል ማለታቸውን የትምህርት ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

በትምህርት ሴክተሩም ይሁን እንደ ሀገር እየተተገበሩ ያሉ ሪፎርሞች በትክክልና በፍትሃዊነት ተግባራዊ እንዲደረጉ በማድረግ ለነገው ትውልድ የተሻለች ሀገር ማስረከብ ይኖርብናልም ነው ያሉት፡፡

 

 

 

Exit mobile version