Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ከግለሰቦች የተያዘ አደንዛዥ ዕጽ ቀንሶ በመሰወር የተከሰሰው የፖሊስ አባል በጽኑ እስራትና ገንዘብ ተቀጣ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 19፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ከግለሰቦች የተያዘን አደንዛዥ ዕጽ ቀንሶ ሰውሯል በሚል የተከሰሰው የፖሊስ አባል በጽኑ እስራትና በገንዘብ ተቀጥቷል፡፡

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ረዳት ኢንስፔክተር ታምራት ታደሰ ለማ በተባለ የፖሊስ አባል ላይ የቀረቡ ማስረጃዎችን መርምሮና አመዛዝኖ የጥፋተኝነት ፍርድ በመስጠት የጽኑ እስራትና የገንዘብ ቅጣት ውሳኔ ወስኖበታል።

በፍትሕ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በተከሳሹ ላይ የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 15(1) እና (2) ስር የተመለከተውን መተላለፍ የሚል ክስ በ2016 ዓ.ም አቅርቦበት ነበር።

በዚህም ተከሳሹ በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ በህብረት ምርመራና ማስተዳደር ዋና ክፍል ስር የአደገኛ ዕጽ ኤግዚቪት አስተዳደር ስራ እንዲሰራ ተመድቦ በመስራት ላይ እያለ በ2015 ዓ.ም በተለያዩ ወራት ከተለያዩ 8 ተጠርጣሪዎች ላይ የተያዙ የተለያየ መጠን ያላቸው የኮኬይን አደንዛዥ ዕጾችን በኤግዚቪትነት ከተረከበ በኋላ በአጠቃላይ ተከሳሽ በአደራ የተረከበዉን ከተጠርጣሪዎች እጅ የተያዘን እና በኤግዚቪትነት የተመዝገበ አደገኛ የኮኬይን ዕጽ ማለትም 7 ጥቅል ፍሬ፣ ከ8 ግለሰቦች የተያዘ 16 ነጥብ 275 ኪሎ ግራም ካናቢስ ዕጽ አጥፍቶ አይነቱን በሌላ ንጥረ ነገር የቀየረ በመሆኑ በፈጸመው በስራ ተግባር የሚፈጸም የመውስድና የመሰወር ወንጀል ተከሷል።

ተከሳሹ የክስ ዝርዝሩ ከደረሰው በኋላ ጠበቃ የማቆም አቅም እንደሌለው መግለጹን ተከትሎ ፍርድ ቤቱ የመንግስት ተከላካይ ጠበቃ እንዲቆምለት ትዕዛዝ የሰጠ ሲሆን÷ በዚህ መሰረትም በተከላካይ ጠበቃ ተወክሎ በክስ ዝርዝሩ ላይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት አለመፈጸሙን ጠቅሶ የዕምነት ክህደት ቃሉን ሰጥቷል፡፡

ከሳሽ ዐቃቤ ሕግም ለወንጀሉ መፈጸም ያስረዱልኛል ያላቸውን በአደንዛዥ እጽ መከላከል የተሰማሩ አባላትን አስቀርቦ ምስክርነታቸውን አሰምቶ ነበር፡፡

ፍርድ ቤቱም የምስክር ቃሉን መርምሮ ተከሳሹ በተከሰሰበት ድንጋጌ ስር እንዲከላከል ብይን የሰጠ ሲሆን÷ተከሳሹ የመከላካያ ማስረጃ ያቀረበ ቢሆንም ያቀረበው መከላከያ ግን የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን መከላከል (ማስተባበል)አለመቻሉ ተጠቅሶ የጥፋተኝነት ፍርድ ተላልፎበታል፡፡

ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኝ የቅጣት አስተያየት መርምሮ ተከሳሹ በኩል የቀረቡ የቅጣት ማቅለያ አስተያየቶችን በመያዝ በ3 ዓመት ከ7 ወራት ጽኑ እስራትና በ2 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ወስኗል።

በታሪክ አዱኛ

Exit mobile version