Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር) በሩሲያና ማሌዢያ የነበራቸው የሥራ ጉብኝት ስኬታማ ነበር- ቢልለኔ ስዩም

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 18፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በብሪክስ የመሪዎች ጉባዔ እና በማሌዢያ በነበራቸው ይፋዊ የስራ ጉብኝት ስኬታማ ቆይታ ማድረጋቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ሃላፊ ቢልለኔ ስዩም ገለጹ።

ቢልለኔ ስዩም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በብሪክስ የመሪዎች ጉባዔ እና በማሌዢያ የነበራቸውን የሥራ ጉብኝት አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም በሩሲያ ካዛን ከተማ የተካሄደው 16ኛው የብሪክስ የመሪዎች ጉባዔ ኢትዮጵያ አባል ከሆነች በኋላ የተሳተፈችበት የመጀመሪያው ጉባዔ መሆኑን  ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በጉባዔው ላይ፣ በሁለትዮሽ እና በባለብዝሃ ወገን የምክክር መድረኮች ላይ ውጤታማ ተሳትፎ ማድረጋቸውን  አመልክተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉባዔው ላይ አፍሪካ በተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ ውክልና ማግኘት እንዳለባት እና ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ስርዓቱ እንዲሻሻል ጥሪ ማቅረባቸውን ተናግረዋል።

ከጉባዔው ጎን ለጎን ከብሪክስ አባል እና አባል ለመሆን ከሚፈልጉ ሀገራት መሪዎች ጋር በተደረጉ የሁለትዮሽ ውይይቶች በማድረግ የኢትዮጵያን አቋሞች ማንጸባረቃቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማሌዢያ በነበራቸው ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ከአገሪቷ ጠቅላይ ሚኒስትር አንዋር ኢብራሂም ጋር መወያየታቸውን ተናግረዋል፡፡

በውይይቱ ወቅት የሁለቱን ሀገራት ለረጅም ጊዜ የቆየ ወዳጅነት ይበልጥ ለማጠናከር የጋራ መግባባት ላይ መደረሱን ጠቁመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የማሌዢያ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ያለውን ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢ አየር ተጠቅመው በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ ማቅረባቸውን አመልክተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ከውይይታቸው ጎን ለጎን የፕሮቶን የመኪና መገጣጠሚያ ማዕከል እና ከተማን የማዘመን ሥራዎችን ጨምሮ የተለያዩ የልማት እንቅስቃሴዎችን መጎብኘታቸውን ተናግረዋል።

በአጠቃላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በብሪክስ የመሪዎች ጉባዔ እና በማሌዢያ በነበራቸው ጉብኝት ስኬታማ ቆይታ አድርገዋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

Exit mobile version