የሀገር ውስጥ ዜና

የምክር ቤቱ 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ስብሰባ ነገ ይካሄዳል

By Mikias Ayele

October 28, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 18፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ስብሰባ ነገ ይካሄዳል፡፡

ምክር ቤቱ በስብሰባው የምክር ቤቱን 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 1ኛ መደበኛ ስብሰባ ቃለ ጉባዔ መርምሮ እንደሚያጸድቅ ይጠበቃል፡፡

በዕለቱ የኢፌዲሪፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ መስከረም 27 ቀን 2017 ዓ.ም ለሕዝብ ተወካዮችና ለፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ መደበኛ ስብሰባ ያደረጉትን የመክፈቻ ንግግር አስመልክቶ የቀረበውን የድጋፍ ሞሽን ማዳመጥ እና የሚኒስትሮችን ሹመት መርምሮ ያጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።

በተጨማሪም  የከተማ መሬትን በሊዝ ለመያዝ የቀረበ ረቂቅ አዋጅን ፣ የከተማ መሬት ይዞታ እና መሬት ነክ ንብረት ለመመዝገብ የቀረበ ረቂቅ አዋጅን እና የአጠቃላይ ትምህርት ረቂቅ አዋጅን መርምሮ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ይመራል።

እንዲሁም ምክር ቤቱ የመገናኛ ብዙሃን ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ይመራል ተብሎ እንደሚጠበቅ የምክር ቤቱ መረጃ መላክታል፡፡