አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 18፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የፍትሕ ሚኒስቴር ሂል ከተሰኘ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ጋር የማሕበረሰብ አቀፍ ፍትሕን ማጠናከር የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል፡፡
ስምምነቱን የፍትሕ ሚኒስቴር የተቋም ግንባታና ሪፎርም ዘርፍ ሚኒስትር ዴዔታ ኤርሚያስ የማነብርሃን(ዶ/ር) እና የሂል ዋና ሥራ አስፈፃሚና መስራች ሳሙኤል ሙለር (ዶ/ር) ተፈራርመዋል፡፡
በስምምነቱ የማህበረሰብ አቀፍ ፍትሕን በኢትዮጵያ ለማጠናከር በሚከናወኑ ተግባራት ላይ ስላሉ ምቹ ሁኔታዎች፣ ሊያጋጥሙ ስለሚችሉ ተግዳሮቶችና የመፍትሄ ሃሳቦችን በተመለከተ ውይይት ተደርጓል፡፡
የፍትሕ ሚኒስትር ሃና አርአያስላሴ በዚህ ወቅት÷ የሂል ድርጅት በፍትሕ ዘርፍ ከሌሎች ተቋማት ጋር አብሮ በመስራት ሰፊ ልምድ ያለው በመሆኑ ተቋማቸው ከዚህ ድርጅት ጋር አብሮ በመስራቱ ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በተለይም ድርጀቱ የሶስት ዓመቱ የፍትሕ ትራንስፎርሜሽን እቅድ አንድ አካል በሆነው የማሕበረሰብ አቀፍ ፍትሕ አገልግሎትን በኢትዮጵያ ለማጠናከር በሚያስችሉ ተግባራት ላይ በመሳተፉ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ሳሙኤል ሙለር (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ በኢትዮጵያ የሚስተዋሉ የማሕበረሰብ ችግሮችን ለመፍታት የማህበረሰብ አቀፍ የፍትሕ አገልግሎት ማዕከላት አስፈለጊ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ድርጅታቸው የፍትሕ ዘርፉን ለመደገፍ ከፍትሕ ሚኒስቴር ጋር አብሮ ለመስራት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል መግለጻቸውንም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡