የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ ድንበር ተሻጋሪ የከርሰ-ምድር ውሃ ሃብቷን በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል እየሰራች ነው

By Melaku Gedif

October 28, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 18፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ድንበር ተሻጋሪ የከርሰ-ምድር ውሃ ሃብቷን በአግባቡ ለመለየትና በፍትሐዊነት ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችል ዝርዝር ጥናት እንደሚደረግ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴዔታ አብርሃ አዱኛ (ዶ/ር) እንዳሉት÷ የውሃ ሃብትን በአግባቡ መምራትና ማስተዳደር በዘለቂነት ለመጠቀም ያስችላል።

ኢትዮጵያ የከርሰ ምድርና የገጸ-ምድር ውሃ ሃብቷ በትክክል ጥቅም ላይ እንዲውል የውሃ ምንጮቹን በአግባቡ መለየትና መጠበቅ እንዳለባት በውሃ ሃብት ፖሊሲ ላይ በዝርዝር መቃኘቱን ገልጸዋል።

እየጨመረ የመጣው የህዝብ ቁጥር፣ የአየር ንብረት ለውጥና የከተሞች መስፋፋት በገጸ-ምድር ውሃ ላይ ጫና ሊያሳድሩ እንደሚችሉም ነው ያነሱት።

ይህን ጫና ለመቀነስ ከገጸ-ምድር ውሃ ባለፈ የከርሰ ምድር ውሃ አማራጮችን መለየትና መጠቀም ተገቢ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሰሞኑን ይፋ ባደረገው የገጸ-ምድር አቀማመጥ ካርታ መሰረት ኢትዮጵያ ድንበር ተሻጋሪ የከርሰ ምድር የውሃ ሃብት እንዳላት መመላከቱን ጠቅሰዋል።

ድንበር ተሻጋሪ የከርሰ ምድር ውሃ ሃብቶችን ከጎረቤት አገራት ጋር በፍትሃዊነት ለመጠቀምና ተደጋጋሚ የውሃ እጥረት በሚያጋጥማቸው አካባቢዎች ጥቅም ላይ ለማዋል የውሃ ሃብቱን መገኛ በትክክል ማወቅ ተገቢ ነው ማለታቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡