የሀገር ውስጥ ዜና

በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፍ ያለውን ሌብነት መታገል ይገባል – ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር)

By Shambel Mihret

October 28, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 18፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፍ ያለውን ሌብነት እና ብልሹ አሠራር ባለድርሻ አካላት መታገል አለባቸው ሲሉ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) አሳሰቡ፡፡

የበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ 100 ቀን ሀገራዊ የሪፎርምና ዋና ዋና የኢኮኖሚ አፈፃፀም እንዲሁም የዘርፉ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ተገምግሟል፡፡

በዚሁ ወቅት ሚኒስትሩ እንዳሉት÷ ኢትዮጵያ ባለፉት 100 ቀናት አፈጻጸም በሁሉም ዘርፍ እያስመዘገበች ላለው ዕድገት የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ዘርፉ ሚና የጎላ ነው፡፡

ዘርፉ በሀገሪቱ እየታየ ያለውን ዕድገት በሚፈለገው ልክ እንዲያግዝ በዘርፉ ያለውን ሌብነት እና ብልሹ አሠራር ሁሉም አመራር እና ሠራተኛ እንዲታገል ማሳሰባቸውን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡

የታየውን ለውጥ በተቋም ደረጃ ለማስቀጠልም አሠራርን ማዘመን፣ ብልሹ አሠራርን ማስቀረት፣ የተሽከርካሪ ቁጥርን መጨመርና በመንገድ ደኅንነት ላይ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት በሚያስችል ደረጃ መሥራት እንደሚገባ አቅጣጫ አስቀምጠናል ብለዋል፡፡