Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በኢትዮጵያ የምስራቅ ተጎራባች ክልሎች በአካባቢው አስተማማኝ ሰላም እንዲረጋገጥ እየሠሩ መሆኑ ተመለከተ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 18፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የምሥራቅ ተጎራባች ክልሎች ተቀናጅተው ሰላምን በአስተማማኝ መንገድ በመጠበቅ ልማትና መልካም አሥተዳደር እንዲረጋገጥ የጀመሩትን ሥራ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የድሬዳዋ አሥተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር ተናገሩ።

በኢትዮጵያ የምሥራቅ ተጎራባች ክልሎች የፀጥታና ደኅንነት ከፍተኛ የአመራር አባላት በስትራቴጂክ አመራርነት ላይ በድሬዳዋ ስልጠና እየተሰጠ ነው፡፡

በስልጠናው ላይ የተገኙት የአሥተዳደሩ ከንቲባ ከድር ጁሃር እንደተናገሩት÷ የምስራቅ ተጎራባች የፀጥታና የፍትሕ አካላት ተቀናጅተው የሚያከናውኑት ተግባር የአካባቢውን ሰላምና ፀጥታ በአስተማማኝ መንገድ እንዲረጋገጥ እያስቻለ ነው።

በአካባቢው አስተማማኝ ሰላም መስፈኑ የሀገሪቷ የወጪና ገቢ ንግድ እንዲሳለጥ እና በአካባቢው የሚከናወኑ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች በተሻለ መንገድ እንዲከናወኑ አስችሏል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የድሬዳዋ አሥተዳደር ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ዋና አዛዥ ኮሚሽነር ዓለሙ መግራ በበኩላቸው÷ የምሥራቁ ተጎራባች ክልሎች የጸጥታ አካላት በጋራ ይህን መሰል ስልጠና መካፈላቸው በቀጣይ በተሻለ ጥምረት የተሻለ ሥራ ለመሥራት እንደሚያስችል ገልፀዋል።

ለሁለት ቀናት በሚሰጠው ስልጠና ላይ የሐረሪ ክልል ፖሊስ፣ የምስራቅ ኦሮሚያ ፖሊስ እና የፌደራል ማረሚያ ፖሊስ ከፍተኛ የአመራር አባላት እየተሳተፉ ነው።

Exit mobile version