Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

 የአየር ክልሌ ለሌሎች ሀገራት ጥቃት እንዲውል አልፈቅድም- ኢራቅ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 18፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢራቅ “እስራኤል የአየር ክልሌን ጥሳ በኢራን ላይ ጥቃት ፈጽማለች” ስትል ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ዋና ፀሐፊ እና የፀጥታው ምክር ቤት አቤቱታ አቀረበች፡፡

የኢራቅ መንግሥት በጻፈው የእስራኤልን ድርጊት የሚኮንን ደብዳቤ÷ “እስራኤል ከዓለም አቀፍ ሕግጋት አፈንግጣ የአየር ክልሌን ጥሳ በፈረንጆቹ ጥቅምት 26 ምሽት ላይ በኢራን ወታደራዊ ዒላማዎች ላይ የአየር ጥቃት ፈጽማለች” ብሏል፡፡

ኢራቅ ከጎረቤት ሀገራት ጋር የጋራ ተጠቃሚነትን መሠረት ያደረገ ጥሩ ግንኙነት እንዳላት በደብዳቤው የተገለጸ ሲሆን÷ የአየር ክልሏ ወይም ግዛቷ ለሌሎች ሀገራት ጥቃት እንዲውል እንደማትፈቅድ ማሳሰቧን ስፑትኒክ ኢንተርናሽናል ዘግቧል፡፡

የኢራቅ ጠቅላይ ሚኒስትር መሐመድ ሺዓ አል-ሱዳኒ÷ የኢራቅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሁለትዮሽ እና የስትራቴጂክ አጋርነት ማዕቀፍ ስምምነቶችን በተመለከተ ከአሜሪካ መንግሥት ጋር አፋጣኝ ውይይት እንዲያድርግ መመሪያ መስጠታቸውም ተመላክቷል፡፡

እስራኤል ከትናንት በስቲያ የኢራቅን የአየር ክልል ጥሳ በማለፍ ፈጽማዋለች በተባለው ጥቃት በኢራን፣ ኢራቅ እና ሶሪያ በሚገኙ ከ20 በላይ የኢራን ወታደራዊ ዒላማዎች ላይ ጉዳት ማድረሷን ዘገባው አስታውሷል፡፡

Exit mobile version