Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

እነ ቀሲስ በላይ መኮንን እንዲከላከሉ ብይን ተሰጠ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 18፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ከአፍሪካ ኅብረት ሒሳብ በሐሰተኛ የክፍያ ሠነድ 6 ሚሊየን 50 ሺህ ዶላር ሊያወጡ ሲሉ ተይዘዋል ተብለው በከባድ ማታለል ሙስና ወንጀል የተከሰሱት እነ ቀሲስ በላይ መኮንን እንዲከላከሉ ብይን ተሰጠ፡፡

ዛሬ ብይኑን የሰጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው።

የፍትሕ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ቄስ በላይ መኮንን፣ በግብርና ኢንቨስትመንት ላይ የተሰማራው እያሱ እንዳለ፣ በኮሚሽን ስራ ላይ የተሰማራው በረከት ሙላቱ እና አለምገና ሳሙኤል እና የኒሞና ንግድ ስራ ኃላ/የተ/የግል ማህበር ስራ አስኪያጅ አበራ መርጋ በተባሉ ተከሳሾች ላይ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ ቁጥር 32 ንዑስ ቁጥር 1(ሀ) እና የሙስና ወንጀሎች ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀፅ 32 ንዑስ ቁጥር 2 እና ንዑስ ቁጥር 3 ስር የተመለከተውን ድንጋጌ እና በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ህግ ቁጥር 382 ንዑስ ቁጥር 1 ስር የተመለከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ ከአፍሪካ ህብረት ምንም አይነት የክፍያ ትዕዛዝ ባልተሰጠበት ሁኔታ ላይ ከ2ኛ እስከ 5ኛ ተራ ቁጥር ለተከሰሱ ተከሳሾች በተለያየ የዶላር መጠን ክፍያ እንዲፈጸምላቸው የሚል አጠቃላይ የ 6 ሚሊየን 50 ሺህ ዶላር ሐሰተኛ የክፍያ ሠነድ በአንደኛ ተከሳሽ መቅረቡ ተጠቅሶ በሁሉም ተከሳሾች ላይ ከባድ የማታለል ሙስና ወንጀል ክስ መመስረቱ ይታወሳል።

በዚህ መልኩ የቀረበውን ክስ ከ1ኛ እስከ 3 ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱት ብቻ ችሎት የቀረቡና የክስ ዝርዝሩ እንዲደርሳቸው የተደረገ ሲሆን÷ 4ኛ እና 5ኛ ተከሳሾች በአድራሻቸው ባለመገኘታቸውና በተደጋጋሚ ቀጠሮ ባለመቅረባቸው ለጊዜው ክሳቸው እንዲቋረጥ ተደርጓል።

ከ1ኛ እስከ 3ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ተከሳሾች ክሱ እንዲሻሻልላቸው ያቀረቡት የመጀመሪያ ደረጃ ክስ መቃወሚያ ነጥቦችን ፍርድ ቤቱ መርምሮ ወደፊት በማስረጃ እንደሚጣራ ገልጾ መቃወሚያቸውን አልተቀበለውም።

በክሱ ላይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት አለመፈጸማቸውን ጠቅሰው ተከሳሾቹ የዕምነት ክህደት ቃላቸውን መስጠታቸውን ተከትሎ ዐቃቤ ህግ የአፍሪካ ኅብረት ቅርጫፍ የባንክ ባለሙያዎችን አጠቃላይ 3 ምስክሮችን አቅርቦ ምስክርነታቸውን አሰምቶ ነበር፡፡

ፍርድ ቤቱ ዐቃቤ ህግ ያሰማቸውን የምስክሮችን ቃልና የሰነድ ማስረጃዎችን መርምሮ በአንደኛው ክስ እንዲከላከሉ በሙሉ ድምጽ ብይን ሰጥቷል።

ሁለተኛውን ክስ በሚመለከት በሐሰተኛ ሠነድ የተፈጸመ ድርጊት መሆኑ በአንደኛውን ክስ ላይ መገለጹን ተከትሎ በሰበር ሰሚ ችሎት ትርጉም የተሰጠባቸው በተደራራቢነት የቀረቡና ተጠቃልለው ሊያስቀጡ የሚችሉ ድንጋጌዎች መኖራቸውን ፍርድ ቤቱ አብራርቶ ሁለተኛውን ክስ ውድቅ በማድረግ በአንደኛው ክስ ብቻ በከባድ አታላይነት ሙስና ወንጀል እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቷል።

ተከሳሾቹ የመከላከያ ማስረጃ ካላቸው ለመጠባበቅ ለሕዳር 16 ቀን 2017 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ

Exit mobile version