Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የኢትዮጵያና ቻይናን ጽኑ ወዳጅነት ለማስጠበቅ እንሠራለን- የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 18፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ እና ቻይና መካከል ለዓመታት የቀጠለውን ጽኑ ወዳጅነት ለማስጠበቅ እንደሚሠራ የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ አስታወቀ፡፡

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ የተመራ ልዑክ ከቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምክትል ሚኒስትር ሊ ሚንሽያንግ ጋር ተወያይቷል፡፡

በዚሁ ወቅት የፓርቲ ለፓርቲ፣ የመንግሥት ለመንግሥት እና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን በይበልጥ ለማጠናከር የሚያስችሉ ሐሳቦችና በቀጣይ ሊሠሩ በታሰቡ ስትራቴጂያዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት ላይ መድረሳቸው ተገልጿል፡፡

ቻይና እና ኢትዮጵያ ረጅም ታሪክ ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን በማውሳት በሁሉም ዘርፎች ጠንካራ ግንኙነት መመስረታቸውን አቶ አደም አስገንዝበዋል፡፡

መንግሥት በዋና ዋና ጉዳዮች ላይ እየሠራቸው ስላሉ ሥራዎችና ስለተገኙ ውጤቶች፣ በፓርቲ እየተከናወኑ ስላሉ የአቅም ግንባታና ሪፎርም ጥረቶች እና እየተገኙ ስላሉ ፋይዳዎች እንዲሁም ስለአካባቢያዊና ቀጣናዊ ጉዳዮች አብራርተዋል፡፡

በተጨማሪም የፓርቲ ለፓርቲ ግንኙነቱ በልምድ ልውውጥ፣ በትምህርትና ስልጠና እንዲሁም በሌሎች የአቅም ግንባታ ድጋፎች ተጠናክሮ መቀጠሉን እና ወደ ፊትም ይበልጥ አብረው ለመስራት ብልጽግና ፓርቲ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

ሊ ሚንሽያንግ በበኩላቸው÷ በኢትዮጵያ እና ቻይና መካከል ለዓመታት የቀጠለውን ጽኑ ወዳጅነት ለማስጠበቅ እንሠራለን ሲሉ ማረጋገጣቸውን የብልጽግና ፓርቲ መረጃ አመላክቷል፡፡

ሁለቱ ፓርቲዎች የገነቡት የረጅም ጊዜ ትብብርም የመንግሥት ለመንግሥት ግንኙነቱን በሚያጠናክር ደረጃ መድረሱንን አንስተዋል።

Exit mobile version