አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 18፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ለንግድና ኢንቨስትመንት መሬት ወስደው ወደ ልማት ባልገቡ ከ30 በላይ ፕሮጀክቶች ላይ ርምጃ መወሰዱን የሲዳማ ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ፡፡
የቢሮው ኃላፊ ወሰንየለህ ስምኦን በሰጡት መግለጫ÷ የክልሉ መንግሥት የንግድና ኢንቨስትመንት መሬቶች ላይ ጥናት ሲያካሂድ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡
በጥናቱ ውጤት መሠረትና የጥናት ቡድኑ ባቀረበው ምክረ ሐሳብ ላይ የክልሉ መሥተዳድር ምክር ቤት ምክክር ካደረገ በኋላ መሬት ወስደው ወደ ልማት ባልገቡ ፕሮጀክቶች ላይ ርምጃ መውሰዱን ገልጸዋል፡፡
በዚሁ መሠረት መሥተዳድር ምክር ቤቱ በማዕከላዊ ሲዳማ ዞን በሎካ አባያ ወረዳ ቡክቶ በሚባል ሥፍራ በስድስት ፕሮጀክቶች የተያዘው ከ1 ሺህ 500 ሔክታር በላይ ወደ መሬት ባንክ እንዲገባ ወስኗል ብለዋል፡፡
በሐዋሳ ከተማ አሥተዳደር ከዚህ ቀደም ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው የነበሩ 27 ፕሮጀክቶች በጥሩ እንቅስቃሴ ላይ መሆናቸው ጠቅሰው÷ በሌላ በኩል በተለያየ ምክንያት ዘግይተው ግንባታ የጀመሩ 32 ፕሮጀክቶች የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው ሥራቸውን በፍጥነት እንዲጠናቀቁ መሰወኑን አንስተዋል፡፡
ከዚህ ቀደም የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው እንዲሁም ምንም እንቅስቃሴ እንደሌላቸው የተገመገሙ 25 ፕሮጀክቶች የያዙት መሬት ወደ መሬት ባንክ እንዲገባ ተወስኗል ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ አመላክቷል፡፡
በቀጣይም መሬት ወስደው በተያዘላቸው ጊዜ እና ዕቅድ ወደ ልማት በማይገቡት ላይ የሚወሰደው ርምጅ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡