ቢዝነስ

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከማዕድን የወጪ ንግድ ከ207 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ

By Tibebu Kebede

July 15, 2020

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 8፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከተለያዩ ማዕድናት የወጪ ንግድ ከ207 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ አግኝታለች።

በማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር የማዕድን ግብይት ስራዎች ብቃት ማረጋገጥ ዳይሬክተር አቶ በትሩ ኃይሌ ለኢዜአ እንደገለጹት በ2012 በጀት ዓመት ከዘርፉ ለማግኘት የታቀደው ገቢ ከ260 ሚሊየን ዶላር በላይ ነው።

ያም ሆኖ የተገኘው ገቢ ካለፈው ዓመት አጠቃላይ ገቢ ከ159 ሚሊየን ዶላር በላይ ብልጫ እንዳለው ገልጸዋል።

ከወርቅ ብቻ የተገኘው ገቢ በ2011 በጀት ዓመት ከተገኘው ከ30 ሚሊየን ዶላር የማይበልጥ ገቢ ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ መሻሻል እንዳለውም ተናግረዋል።

ለገቢው መጨመር ደግሞ መንግስት የኮሮና ወረርሽኝ በምጣኔ ሃብት ላይ የሚያስከትለውን መቀዛቀዝ ለመቋቋም በወርቅ ላይ ያደረገው የዋጋ ማስተካከያ ምክንያት መሆኑን ጠቅሰዋል።

በተወሰነ ደረጃ የሃገሪቷ ድንበሮች መዘጋታቸውን ተከትሎ የኮንትሮባንድ ንግድ በመቀነሱ ወደ ባንክ የሚገባው የወርቅ መጠን መጨመሩም ሌላው ምክንያት መሆኑን ጠቅሰዋል።

በወርቅ የወጪ ንግድ ገቢ የተሻለ አፈጻጸም ቢመዘገብም ማዕድናት በተለይም ጌጣጌጥና ታንታለም ወደ ውጭ በሚልኩ ነጋዴዎች ላይ የአየር ትራንስፖርት መቋረጥና የገበያ መቀዛቀዝ ጫና መፍጠሩንም አውስተዋል።

ኢትዮጵያ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከማዕድን ዘርፍ ያገኘችው የውጭ ምንዛሬ ከ2004 በጀት ዓመት ወዲህ ከፍተኛው ነው ተብሏል።