የሀገር ውስጥ ዜና

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብና የምክክር ምዕራፍ ተጀመረ

By Shambel Mihret

October 28, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 18፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ እና የምክክር ምዕራፍ ሒደትን አስጀምሯል።

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር)÷መሰረታዊ የሃሳብ ልዩነቶችና አለመግባባቶች እየሰፉ በመምጣታቸው ኮሚሽኑ እነዚህን ልዩነቶች በምክክር ለመፍታት ይቻል ዘንድ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልልም ለምክክር የሚቀርቡ አጀንዳዎች በውይይቱ እንደሚሰባሰቡ ጠቁመው÷ሒደቱ አሳታፊ፣ አካታችና ተዓማኒ እንደሚሆንም ተናግረዋል።

እስካሁን በ7 ክልሎችና 2 ከተማ አስተዳደሮች ከ932 ወረዳዎች የተውጣጡ 105 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች በአጀንዳ ማሰባሰብ ሒደቱ መሳተፋቸውን አንስተዋል፡፡

በአማራ እና ትግራይ ክልሎች የአጀንዳ ማሰባሰቡን ለማካሄድ ዝግጅቶች እየተደረጉ እንደሆነም ኮሚሽኑ አመላክቷል፡፡

በዘመን በየነ