አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 18፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካ ለታይዋን የፈጸመችው የ2 ቢሊየን ዶላር የጦር መሳሪያ ሽያጭ ውል የቻይናን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት የጣሰ ነው ስትል ቤጂንግ ከሰሰች፡፡
የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው÷ቻይና በአሜሪካና ታይዋን የተፈጸመውን የ2 ቢሊየን ዶላር የጦር መሳሪያ ሽያጭ ውል ስምምነት አጥብቃ ታወግዛለች፡፡
ስምምነቱ የአሜሪካ እና ቻይናን ግንኙነት ይጎዳዋል ያለው ሚኒስቴሩ÷ቤጂንግ ሉዓላዊነቷን እና የግዛት አንድነቷን ለማስጠበቅ አስፈላጊውን እርምጃ እንደምትወስድ አረጋግጧል፡፡
የ2 ቢሊየን ዶላር ዋጋ ያላቸው ጦር መሳሪያዎቹ የታይዋንን አየር ሃይል ለማጠናከርና የቀጣናውን ሰላም ለማስጠበቅ እንደሚውሉ ነው የተገለጸው፡፡
በስምምነቱ መሰረት የአሜሪካ አየር ሃይል ለታይዋን ዘመናዊ የአየር መከላከያ መሳሪያዎችን እንደሚያቀርብ የተጠቆመ ሲሆን÷ የሁለቱ ሀገራት የጦር መሳሪያ ሽያጭ በቅርቡ በአሜሪካ ኮንግረስ እንደሚፀድቅ ይጠበቃል፡፡
ታይዋን ስምምነቱ የሀገሪቱን የመከላከል አቅም የሚያጠናከር እና የፓስፊክ ቀጣናን ደህንነት እንደሚያስጠብቅ ገልጻ÷ለአሜሪካ መንግስትም ምስጋና አቅርባለች፡፡
ቻይና የግዛቴ አንድ አካል የምታላት ታይዋን ከአሜሪካ ጋር የምታደርገው ግንኙነት ሉዓላዊነቷን የሚጥስ ቀይ መስመር እንደሆነ በተደጋጋሚ ስትገልጽ ቆይታለች፡፡
ታይዋን ከድርጊቷ ካልተቆጠበችም ወታደራዊ እርምጃ እንደምትወስድ ስታስጠነቅቅ መቆየቷን አልጀዚራ በዘገባው አስታውሷል፡፡