አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 18፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ባሕር ዳር ኢንዱስትሪ ፓርክ በግብርና ዘርፍ ለተሰማሩ ባለሀብቶች፣ ለአምራች አርሶ አደሮች እና ለሥራ ፈላጊ ወጣቶች ተጠቃሚት ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑ ተገለጸ፡፡
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የኢንቨስትመት ፕሮሞሽን እና ማርኬቲንግ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዘመን ጁነዲን ፓርኩ በአግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፍ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ለአብነትም በፓርኩ ውስጥ ሥራ ከጀመሩ ኢንቨስትመንቶች መካከል ኒርቫና ለ10 ሺህ አኩሪ አተር አምራች አርሶ አደሮች ዘላቂ የገበያ ትስስር መፍጠሩን ጠቅሰዋል፡፡
እንዲሁም ሌላኛው በፓርኩ ሥራ የጀመረ አፉላንስ ማኑፋክቸሪንግ ኩባንያ የኤሌክትሪክ ትራንስፎርመሮችን በማምረት ከክልሉ አልፎ ለተለያዩ የሀገሪቱ ከፍሎች ምርቶቹን እያቀረበ ነው ብለዋል፡፡
በዚህም ለአካባቢው ወጣቶች የሥራ ዕድል ከመፍጠሩ በተጨማሪ በቴክኖሎጂ እና እውቀት ሽግግር ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ ነው ማለታቸውንየኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን መረጃ አመላክቷል፡፡
በፓርኩ ለመሰማራት አቅሙና ፍላጎቱ ያላቸው የሀገር ውስጥ እና የውጪ ባለሀብቶችን ለማስተናገድ የሚያስችሉ መሰረተ ልማት የተሟላላቸው የማምረቻ ሼዶችና የለማ መሬት ዝግጁ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የፓርኩ ሥራ አስኪያጅ ጥሩዬ ቁሜ ናቸው፡፡