Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በማደግ ላይ ላሉ ሀገራት ፍትሐዊ የፋይናንስ አቅርቦት እንዲኖር መሥራት ይገባል – አቶ አሕመድ ሽዴ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 17፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ኢትዮጵያ እና ሌሎች በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራት ፍትሐዊ የፋይናንስ አቅርቦት እንዲያገኙ መሥራት እንደሚጠበቅበት የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ አስገነዘቡ።

በዋሺንግተን ዲሲ እየተካሄደ ካለው የዓለም ባንክ እና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ) ዓመታዊ ስብሰባ ጎን ለጎን የቡድን ሰባት እና የአፍሪካ (G-7 Africa) የሚኒስትሮች ስብሰባ ተደርጓል።

በአቶ አሕመድ ሽዴ የተመራ ልዑክም በስብሰባው ላይ ተሳትፏል።

ጣሊያን በፕሬዚዳንትነት የምትመራው የቡድን ሰባት የፋይናንስ ሚኒስትሮች በእዳ አስተዳዳር ላይ ያሉ ፈተናዎች፣ በአፍሪካ የፋርማሲዩቲካል አምራች ዘርፍ ላይ ያሉ ኢኒሼቲቮች፣ አረንጓዴ መሰረተ ልማት እንዲሁም ሁሉን አቀፍ እና የማይበገር የአቅርቦት ሰንሰለት አስመልክቶ ውይይት አድርገዋል።

አቶ አሕመድ በስብሰባው ላይ ባደረጉት ንግግርም፥ ኢትዮዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አመራር ሰጪነት ታሪካዊ እና ቆራጥነት የተሞላበት የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራሞችን እየተገበረች እንደምትገኝ ገልጸዋል።

ማሻሻያው የማክሮ ኢኮኖሚ ፈተናዎችን ለመፍታት እና ከመንግስት መር ወደ ግል መር ኢንቨስትመንት በመሸጋገር ሚዛናዊ የእድገት ምንጭ መፍጠርን ታሳቢ ያደረገ ነው ብለዋል።

ሪፎርሙ የሀገር ውስጥ የሀብት መሰብሰብ አማራጭ ማስፋት፣ የወጪ አጠቃቀምን ለከት ለማስያዝ እና ጥብቅ የፊስካል ስርዓትን በመፍጠር ዘላቂ የፊስካል አስተዳደር ስርዓትን ማረጋገጥ እንደሚያስችል አመልክተዋል።

የውጭ ምንዛሪ ስርዓቱን በገበያ እንዲመራ በማድረግ ያሉ ችግሮችን ለማስተካከል እንደሚረዳም ተናግረዋል።

የተቋማት እና በተለያዩ ዘርፎች እየተደረጉ ያሉ ማሻሻያዎች ምርታማነትን ለማሳደግ፣ ለስራ እድል ፈጠራ እና የኢኮኖሚ እድገትን ለማሳለጥ ምቹ መደላድል ይፈጥራል ነው ያሉት ሚኒስትሩ።

የኢትዮጵያ መንግስት ለዘላቂ እድገት ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸው፥ ለኢትዮጵያ እና ሌሎች በማደግ ላይ ለሚገኙ ሀገራት ዝቅተኛ የወለድ ምጣኔ ያለው የፋይናንስ አቅርቦት እንዲያገኙ እየተደረገ ላለው ድጋፍ ቀጣይነት ያለው ዓለም አቀፍ ትብብር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

በሚኒስትሮቹ ስብሰባ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለአፍሪካ መር፣ ሀገር በቀል ለሆኑ ማሻሻያዎች እና የኢንቨስትመንት እቅዶች እንዲሁም የአፍሪካ ሀገራት ሀገር በቀል የፋይናንስ ማሰባሰብ አቅማቸውን በማጎልበት የፊስካል እፎይታ እንዲያገኙ እና የረጅም ጊዜ የልማት ስራቸውን ለመደገፍ እያከናወኑት ያለውን ስራ በተጠናከረ መልኩ እንዲደግፍ ጥሪ ቀርቧል።

በስብሰባው ላይ የቡድን ሰባት አባል ሀገራት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የአፍሪካ የፋይናንስ ሚኒስትሮች እና የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ተወካዮች መገኘታቸውን ከገንዘብ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ አመላክቷል።

 

Exit mobile version