የሀገር ውስጥ ዜና

ለአየር ኃይል ከ32 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የግንባታ ቁሳቁሶች ድጋፍ ተደረገ

By Shambel Mihret

October 27, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 17፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የገቢዎች ሚኒስቴር እና የጉምሩክ ኮሚሽን ለአየር ኃይል የሰራዊቱ መኖሪያ ቤት ግንባታ የሚሆን ከ32 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጡ የግንባታ ቁሳቁሶችን ድጋፍ አድርገዋል፡፡

ድጋፉን የገቢዎች ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሴ እና የጉምሩክ ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ ለአየር ኃይሉ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል ይልማ መርዳሳ ቢሾፍቱ አየር ኃይል ግቢ ተገኝተው አስረክበዋል።

በዚሁ ወቅት ወ/ሮ ዓይናለም ንጉሴ÷የመከላከያ ሰራዊት ብሎም የአየር ኃይል የኢትዮጵያ የተቋማት ግንባታ ተምሳሌቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።

አየር ኃይሉ ሁሉንም ኢትዮጵያውያን ያቀፈ ተቋም መሆኑን ጠቅሰው÷የተደረገው ድጋፍ ተቋሙ የጀመረውን የሪፎርም ስራ ለማገዝ እንደሚረዳ ተናግረዋል።

ኮሚሽነር ደበሌ በበኩላቸው÷ በአየር ኃይሉ እየተከናወነ የሚገኘው ሪፎርም ለሌሎች ተቋማት ምሳሌ የሚሆን እና አኩሪ ተግባር ነው ብለዋል።

ሌተናል ጀነራል ይልማ መርዳሳ ÷በሰው ኃይል፣ በትጥቅ እና በስነ ልቦና የተጠናከረ ኃይል ለመገንባት እየተሰራ መሆኑን ገልፀው የተደረገው ድጋፍም ለሰራዊቱ የመኖሪያ ቤት ግንባታ እንደሚውል ተናግረዋል፡፡

ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎቹ በአየር ኃይሉ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎችንም መጎብኘታቸውን የገቢዎች ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡