የሀገር ውስጥ ዜና

በክልሉ ሥራ አጥነትን ለመቅረፍ እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ

By Mikias Ayele

October 27, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 17፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የዜጎችን የሥራ አጥነት ችግር ለመፍታት በትኩረት እየተሠራ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ጥላሁን ከበደ አስታወቁ፡፡

የክልሉ የሥራ ዕድል ፈጠራ እና ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ የሥራ ዕድል ፈጠራ ተግዳሮቶችና መፍትሔዎች ላይ ያተኮረ ክልላዊ የንቅናቄ መድረክ በወላይታ ሶዶ ከተማ አካሂዷል፡፡

ርዕሰ መሥተዳድሩ በዚሁ ወቅት በክልሉ ዘላቂ፣ አስተማማኝና ፍትሐዊ የሥራ ዕድል ፈጠራ እና ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ እየተሠራ መሆኑ ተናግረዋል፡፡

የሥራ ዕድል ፈጠራ በቅንጅት የሚሠራ እንጂ በአንድ አካል ብቻ የሚከናወን አለመሆኑን በመገንዘብ በየደረጃው የሚገኙ መዋቅሮች እና የዘርፉ ኃላፊዎች ለዘርፉ ስኬት ርብርብ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ምክትል ርዕሰ መሥተዳደር እና የሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ ኃላፊ ገብረ መስቀል ጫላ በመድረኩ ላይ በበኩላቸው ÷ የሥራ ዕድል ፈጠራ የኢኮኖሚ ሥርዓት ጤነኝነት ማስጠበቂያ ነው፡፡

ሁሉም ሥራ የሚፈልጉ ዜጎች ስልጠና እንዲያገኙ የማድረግ ክኅሎት መር ተግባር እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የወላይታ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ጴጥሮስ ወልደ ማሪያም ÷ በዞኑ ባለፉት ሦስት ወራት ከ105 ሺህ 559 በላይ ሥራ ፈላጊ ወጣቶች ተለይተዋል ብለዋል፡፡

በዚህም 1 ሺህ 763 ሔክታር መሬት በግብርና ዘርፍ ለተሰማሩ ወጣቶች መሰጠቱን እና ለ8 ሺህ 427 ወጣቶች ቋሚ የሥራ ዕድል መፈጠሩን ተናግረዋል፡፡

በመለሰ ታደለ እና ማቴዎስ ፈለቀ