ዓለምአቀፋዊ ዜና

በፊሊፒንስ በመሬት መንሸራተት የ81 ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ 25 ዜጎች የገቡበት አልታወቀም

By Mikias Ayele

October 27, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 17፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በሰሜን ምዕራብ ፊሊፒንስ ከባድ ዝናብ ባስከተለው የመሬት መንሸራተት የ81 ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ ተጨማሪ 25 ዜጎች የገቡበት አለመታወቁ ተሰምቷል፡፡

አደጋው ባልተለመደ መልኩ ለ24 ሰዓት የጣለውን ከባድ ዝናብ ተከትሎ መከሰቱን የገለጹት የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ፈርዲናንድ ማርከስ÷ የሟቾች ቁጥር ሊያሻቅብ እንደሚችል አመላክተዋል፡፡

ከ5ሚሊየን በላይ ሰዎች የአደጋው ተጠቂ ሊሆኑ እንደሚችሉ ገልጸው÷ እስከ አሁን ከግማሽ ሚሊየን በላይ ዜጎች በጊዜያዊ መጠለያዎች እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡

ከአደጋው ጋር በተያያዘም የተጎጅዎች ቁጥር የከፋ እንዳይሆን መንግሥት ትምህርት ቤቶችን ለሦስት ቀናት እንዲዘጉ መወሰኑን ሲ ጂቲኤን ዘግቧል፡፡

የገቡበት ያልታቁ 25 ዜጎችን ለማግኘት የሀገሪቱን ፖሊስ ጨምሮ የነፍስ አድን ሠራተኞች እና አነፍናፊ ውሾች የማፈላለግ ሥራ እያከናወኑ ነው ብለዋል፡፡