የሀገር ውስጥ ዜና

ዴንማርክ በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር መስራቷን አጠናክራ እንደምትቀጥል ገለጸች

By amele Demisew

October 26, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 16፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ዴንማርክ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የአየር ንብረት ለውጥ የመከላከል እና የአረንገዴ ልማት ስራዎችን የማስፋፋት ትብብር ይበልጥ ማጠናከር እንደምትፈልግ የሀገሪቱ እጩ አምባሳደር ሱኔ ክሮግስትሮፕ ገልጸዋል።

ዴንማርክ በ29ኛው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 29) ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆኗንም የሀገሪቱ እጩ አምባሳደር ሱኔ ክሮግስትሮፕ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል፡፡

ለዚህም ዴንማርክ ኢትዮጵያ በባኩ የምታቀርበውን የአረንጓዴ ልማት አውደ-ርእይ ትደግፋለች ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘም ኢትዮጵያ ያስመዘገበችው ውጤታማ ተሞክሮ ለዓለም በስፋት መተዋወቅ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

በአዘርባጃን ባኩ ከሕዳር 2 እስከ 13 ቀን 2017 ዓ.ም በሚካሄደው ኮፕ 29 ጉባኤ ለአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ የሚሆን የገንዘብ ድጋፍ ማሰባሰብ በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ምክክር እንደሚደረግ እጩ አምባሳደሩ አስገንዝበዋል፡፡

ኢትዮጵያ በኮፕ 29 ቅድሚያ የምትሰጣቸው ጉዳዮች ከዴንማርክ የአየር ንብረት ለውጥ ግቦች ጋር የተጣጣሙ ናቸው ያሉት እጩ አምባሳደር ሱኔ ክሮግስትሮፕ ÷ ለተፈጻሚነቱም በመንግስታቸው በኩል ያላሰለሰ ድጋፍ እንደሚደረግ ገልጸዋል።

ዴንማርክ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የአየር ንብረት ለውጥ የመከላከል እና የአረንገዴ ልማት ስራዎችን የማስፋፋት ትብብር ይበልጥ ማጠናከር እንደምትፈልግም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ያደጉ ሀገራት በአየር ንብረት ለውጥ ይበልጥ እየተጎዱ ለሚገኙ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ከዚህ ቀደም የገቡትን ቃል ተፈጻሚ እንዲያደርጉ ግፊት በማድረግ ሂደት ሀገራቸው የነቃ ተሳትፎ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗንም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የአየርን ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ያከናወነቻቸው ውጤታማ ተግባራት ለሌሎች ሀገራት በማሳያነት የሚጠቀስ ስለመሆኑም አንስተዋል፡፡

በወንድወሰን አረጋኸኝ