የሀገር ውስጥ ዜና

አቶ አህመድ ሺዴ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በትብብርና የልማት ስራዎች ዙሪያ መከሩ

By Meseret Awoke

October 26, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 16፣ 2017(ኤፍ ቢ ሲ) በገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ የተመራው ከፍተኛ የልኡካን ቡድን ከፈረንሳይ የልማት ኤጀንሲና ከእስያ መሰረተ ልማት ኢንቨስትመንት የስራ ኃላፊዎች ጋር ተወያይቷል።

እየተካሄደ ካለው የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም እና የዓለም ባንክ አመታዊ ስብሰባ ጎን ለጎን የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ ከእስያ መሰረተ ልማት ኢንቨስትመንት ባንክ ፕሬዚዳንት ጂን ሊኩን እና ከፈረንሳይ የልማት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ሬሚ ሪዮክስ ጋር ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም በተለያዩ የትብብርና የልማት ስራዎች ድጋፍ ዙሪያ መክረዋል፡፡

አቶ አህመድ ሺዴ ከፕሬዚዳንት ሊኩን ጋር ባደረጉት ምክክር ፥ ባንኩ ለመሠረተ ልማት የሚሆን ኮንሴንሽናል ፋይናንስ በሚሰጥበት አግባብና ቀጣይ የትብብር ስራዎች ላይ ተገልጿል::

በዚህ ረገድ ፕሬዚዳንት ሊኩን ከአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክና ከአውሮፓ ህብረት ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ የሚከናወኑ የኢነርጂ ፕሮጀክቶችን እንደሚደግፉ አረጋግጠዋል።

እንዲሁም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ በቢሾፍቱ ለመገንባት ላሰበው ግዙፍ ኤርፖርት ፋይናንስ የሚደረግበትን ሁኔታ በቀጣይ ለማየት ከስምምነት መደረሱም ተመላክቷል።

በተጨማሪም ሚኒስትሩ ከፈረንሳይ የልማት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ሬሚ ሪዮክስ ጋር በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ስላሉ የልማት ስራዎች ተወያይተዋል።

በነበራቸው ቆይታም ፥ የፈረንሳይ መንግስት በተለይ ለኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ስለሚሰጠው ተጨማሪ ድጋፍ መምከራቸው የዘገበው ኢዜአ ነው።

በቀጣይም በሁለትዮሽ ትብብር የሚደርገው እገዛ ተጠናክሮ ስለሚቅጥለብት አግባብም መወያየታቸው ተመላክቷል።