የሀገር ውስጥ ዜና

በሐረሪ ክልል አዳዲስ የገጠር ተደራሽ መንገዶችን ለማስፋፋት የሚያስችል ፕሮግራም ይፋ ሆነ

By Meseret Awoke

October 26, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 16፣ 2017(ኤፍ ቢ ሲ) በሐረሪ ክልል አዳዲስ የገጠር ተደራሽ መንገዶችን ለማስፋፋት የሚያስችል ፕሮግራም ይፋ ተደረገ።

የኢፌዴሪ ከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር በሐረሪ ክልል የሚተገበረው የገጠር ትስስርና ተደራሽነት ፕሮግራም ማስጀመሪያ መርሐ-ግብር ተካሂዷል።

በመርሐ-ግብሩ ላይ የሐረሪ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደርና የግብርና ልማት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሮዛ ኡመር እንዳሉት ፥ መንግስት የመሠረተ ልማት ተደራሽነትን በማስፋት በገጠርና በከተማ የሚገኙ ዜጎችን ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል።

ለዚህም በከተሞች የኮሪደር ልማት ተደራሽነትን በማስፋት ከተሞች ለዜጎች ምቹ እንዲሆኑ በመከናወን ላይ የሚገኙ ውጤታማ ተግባራትን ለማሳያነት አንስተዋል።

በከተሞች አካባቢ በመጀመሪያው ዙር በኮሪደር ልማት የተገኘውን ተሞክሮ በመቀመርና በማስፋት በገጠር አካባቢዎችም የኮሪደር ልማት ኢኒሼቲቭ መጀመሩንም አመልክተዋል።

የገጠር ትስስርና ተደራሽነት ለምግብ ዋስትና ፕሮግራም በዋናነት በክልሉ ገጠር ወረዳዎች የምግብ ሉአላዊነትን ለማረጋገጥና የመሰረተ ልማት ተደራሽነትን ለማስፋት የሚያስችል መሆኑን ገልፀዋል።

ፕሮግራሙ በመንግስትና በዓለም ባንክ ድጋፍ በክልሉ ሶፊ ወረዳ ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የሚተገበር ሲሆን ፥ በ58 ሚሊየን ብር 11ኪ.ሜ የሚሸፍን ደረጃውን የጠበቀ መንገድ እንደሚዘረጋ ጠቁመዋል።

ለፕሮግራሙ ስኬታማነት የፕሮግራሙ አስተባባሪ ኮሚቴ አባላትና ባለድርሻዎች የተቀናጀ ድጋፍና ክትትል ማድረግ እንዳለባቸውም መግለጻቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በፕሮግራሙ የማስጀመሪያ መርሐ-ግብር ላይ በፕሮግራሙ ፋይዳና አተገባበር ላይ ትኩረት ያደረገ ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

በመድረኩ የፕሮግራሙ ስትሪንግ ኮሚቴ አባላትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።