አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 16፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የዲላ መካከለኛ አግሮ ኢንዲስትሪ ፓርክ ለመጀመሪያ ጊዜ ያመረተውን 22 ሺህ ሊትር የአቮካዶ ዘይት ምርት ለውጭ ገበያ ማቅረቡን ገለጸ።
በኢንዱስትሪ ፓርኩ የሲይዝ አግሮ ኢንዱስትሪ ማህበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ጌቱ ፥ በአንድ ፈረቃ የተመረተ 22 ሺህ ሊትር የአቮካዶ ዘይት ለመጀመሪያ ጊዜ ለውጭ ገበያ መቅረቡን ገልጸዋል፡፡
በቀጣይ የሚመረትበትን ፈረቃ በማሳደግ በዓመት ለአራት ጊዜ የአቮካዶ ዘይት ለአውሮፓ እና ለአሜሪካ ገበያዎች ለማቅረብ የሚያስችል ትስስር እየተፈጠረ መሆኑንም ተናግረዋል።
ከአቮካዶ ዘይት ምርት በተጨማሪ ቡናን እሴት ጨምሮ ለውጭ ገበያ ለማቅረብና ከአቮካዶ ተረፈ ምርት የእንስሳት መኖ ለማምረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ምርቱ ለውጭ ገበያ መቅረቡ በቀጣይ የፓርኩን ምርታማነትና ተወዳዳሪነት ከማሳደግ ባለፈ በሀገሪቱ ላሉ መሰል ፓርኮች መነሳሳት እንደሚፈጥርም ተገልጿል፡፡
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጥላሁን ብርሃኑ በበኩላቸው ፥ ፓርኩ ቴክኖሎጂ በማሸጋገርና በሥራ ዕድል ፈጠራ ካለው አስተዋጾ ባለፈ የአቮካዶ ዘይት ምርት ለውጭ ገበያ ማቅረብ መጀመሩ በእድገትና ሽግግር ምዕራፍ ላይ እንዲሚገኝ አመላካች ነው ብለዋል።
በቀጣይ አቅሙን በማጠናከር በዓመት ከ130 ቶን በላይ የአቮካዶ ዘይት ምርት ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አመልክተዋል።
ፓርኩ በውስጥ ከፈጠረው የሥራ እድል ባለፈ በግብዓት አቅርቦት ትስስር ከ3 ሺህ በላይ የአካባቢውን አርሶ አደሮች ተጠቃሚ ማድረጉን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡