የሀገር ውስጥ ዜና

የመንግስት ሃብት ለታለመለት ልማት እንዲውል በክልሉ ጠንካራ ክትትል እየተደረገ ነው ተባለ

By Meseret Awoke

October 26, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 16፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመንግስት ሃብት ለታለመለት የልማት ስራ እንዲውል ጠንካራ ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው፣ የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋጤ ስርሞሎና ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት የፋይናንስ ዘርፍ ጉባኤና የንቅናቄ መድረክ በወልቂጤ ከተማ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ ላይ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመሰረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ መሀመድ ኑርዬ(ዶ/ር) ፥ የመንግስትን ሃብት ለታለመለት የልማት ስራ ማዋል እንደሚገባ አመልክተዋል።

ወጪን መቀነስ ላይ ክልሉ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸው ፤ በዚህም የህዝብ የልማት ጥያቄዎች በተያዘላቸው ዕቅድ መሰረት ተፈጻሚ እንዲሆኑ ክትትል እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም በጥሬ ገንዘብ አስተዳደር እንዲሁም የሂሳብ አያያዝ ሪፖርት ወቅታዊነትና ጥራት ረገድ የሚስተዋሉ ጉድለቶችን የማረም ስራ በልዩ ትኩረት እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም የመንግስት ሃብት ለታለመለት ዓላማ እንዲውል ጠንካራ ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።

የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ዘይቱና ኢብራሂም በበኩላቸው እንዳሉት ፥ በክልሉ ያሉትን ሀብቶች በተገቢው መንገድ ለሁሉም ተቋማት ተደራሽ እንዲሆን እየተደረገ ነው።

ያለውን ሀብት በአግባቡ በመጠቀም በክልሉ ሁለንተናዊ ልማት እንዲረጋገጥ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ቢሮው የበኩሉን እየተወጣ መሆኑን ጠቁመዋል።

በመድረኩ በፋይናንስ ሴክተር የ2017 የሩብ ዓመት አፈጻጸም ላይ ትኩረት ያደረገ ሪፖርት ቀርቦ ውይይት እየተደረገበት መሆኑን የዘገበው ኢዜአ ነው።