Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ጤና ሚኒስቴር 2 ነጥብ 2 ሚሊየን አጎበር መሰራጨቱን ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 16፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት ሦስት ወራት የወባ ሥርጭትን ለመቆጣጠር 2 ነጥብ 2 ሚሊየን አጎበር በመላ ሀገሪቱ መሰራጨቱን የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስቴሩ የፀረ-ወባ መድኃቶችንና የአጎበር ሥርጭቶችን በማካሄድ የወባ ወረርሽኝን ለመከላከል የዝግጅት ሥራዎችን በማከናወን ወደ ትግበራ መግበቱም ተጠቁሟል።

በጤና ሚኒስቴር የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር መሪ ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ሕይወት ሰለሞን የወባ ሥርጭትን ለመቆጣጠር ለኅብረተሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች መከናወናቸውንም ገልጸዋል።

በተለይም ከመስከረም እስከ ሕዳር ያሉት ወራት ለወባ ሥርጭት ምቹ በመሆናቸው ኅብረተሰቡ በውሃ ባቆሩና በኩሬ አካባቢዎች ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርግም አስገንዝበዋል።

በዚህ ረገድ ህብረተሰቡ ግንዛቤ እንዲኖረው መሰራቱን ገልጸዋል።

በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከ6 ነጥብ 6 ሚሊየን በላይ ለሆኑ የወባ ተጠርጣሪ ሕሙማን ምርመራ በማድረግ ተህዋሲው የተገኘባቸው 2 ነጥብ 9 ሚሊየን በላይ ዜጎች ተገቢውን ሕክምና እንዲያገኙ መደረጉንም ጠቁመዋል።

በተመሳሳይም በ167 ወረዳዎች በሚገኙ 1 ነጥብ 9 ሚሊየን ቤቶችን በፀረ-ወባ ትንኝ ኬሚካል ርጭት መከናወኑንም ጠቁመዋል።

ኅብረሰተቡ አካባቢን በማጽዳት እና የመከላከያ ዘዴዎችን በመተግበር ራሱን ሊጠብቅ እንደሚገባም መናገራቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

Exit mobile version