አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 16፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ2 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት ገሊላ ማኑፋክቸሪንግ በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ተመርቆ ስራ መጀመሩ ተገለጸ።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ አለማየሁ ሰይፉ በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ እንደተናገሩት፤ በኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚሰማሩ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች ለዜጎች ሰፊ የስራ ዕድል እየፈጠሩ ነው።
ከዚህም ባለፈ ተኪ ምርቶችን በማምረት የውጭ ምንዛሪ ወጪን ለማስቀረት አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደሆነ ተናግረዋል።
በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፖርክ ውስጥ ዛሬ በይፋ ስራ የጀመረው ገሊላ ኃላ.የተ.የግ.ማ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የህጻናት እና የአዋቂዎች ጫማ እንደሚያመርት ገልጸው፤ ኩባንያው በቆዳ ቴክኖሎጂ ሀገራችንን አንድ ደረጃ ከፍ ያደርጋል ብለዋል።
ጫማ ለማምረት ስራ መጀመሩን የኢንዱስትሪ ፖርኮች ልማት ኮርኮሬሽን የማርኬቲንግ እና ፕሮሞሽን ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ዘመን ጁነዲን ገልጸው፤ ጅምሩ የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች በኢንዱስትሪ ፓርኮች ገብተው እንዲሰሩ ምሳሌ እንደሚሆን ጠቅሰዋል።
ከ2 ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ካፒታል የተቋቋመው ገሊላ ማኑፍክቸሪንግ ከ 1 ሺህ በላይ የስራ ዕድል መፍጠሩን የተናገሩት የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ እና ባለቤት በርሄ አሰፋ፤ በውጭ ሀገር የገበያ ትስስር እንደሚፈጥርም መናገራቸውን የኮርፖሬሽኑ መረጃ አመልክቷል።
ኩባንያው ምርቶቹንም ለሀገር ውስጥ ገበያ ከማቅረቡ በተጨማሪ ወደ ተለያዩ ሀገራት እንደሚልክም ገልጸው፤ አሁን ላይ በቀን 2 ሺህ ጥንድ ጫማዎችን እያመረተ መሆኑን ጠቁመዋል።
በሙሉ አቅሙ ስራ ሲጀምርም 4 ሺህ ጫማዎችን እንደሚያመርትና ከ4 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል ይፈጥራል ተብሏል።