Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ምርታማነት ማሳደጊያ ፕሮጀክት ስትሪንግ ኮሚቴ ስብሰባ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 16፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የተቀናጀ የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ምርታማነት ማሳደጊያ ድጋፍና የወጣቶች ሥራ እድል ፈጠራ ፕሮጀክት ስትሪንግ ኮሚቴ ስብሰባ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር)፣ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)፣ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚልን ጨምሮ ሌሎች የሥራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

አብርሃም በላይ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት፥ ፕሮጀክቱ በተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች አካባቢ የመሥኖ ግድብ ፕሮጀክቶችን ግንባታ በማስፋፋት የግብርና ምርትን ምርታማነት ለማሳደግ ያለመ ነው።

ከዚህ ባለፈም ለወጣቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር ዘመናዊ ግብርናን ማሳደግ እንደሚያስችል ተናግረዋል።

በዚህ መሠረትም በፓርኮቹ አካባቢ የአርሶ አደሮችንና ወጣቶችን የግብርና ምርታማነት ማሳደግ የሚያስችሉ የመሥኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተከናወነ መሆኑ ነው የተገለጸው።

ለአብነትም የጊዳቦ፣ ጣባ እና በለቺት የመሥኖ ፕሮጀክቶችን ጨምሮ ሌሎች ተያያዥ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑ ተመላክቷል።

ግርማ አመንቴ ዶ/ር) በበኩላቸው፥ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ምርታማነት ለማሳደግ በአቅራቢያ የሚገኙ አርሶ አደሮች በዘመናዊ ግብርና ታግዘው እንዲሰሩ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

በመስኖ ፕሮጀክቶች ተጠቃሚ የሚሆኑ አርሶ አደሮች የሚያመርቱት ምርት በፓርኮቹ ፍላጎት ላይ የተመሠረተ እንዲሆን በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

ይህም በአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚስተዋለውን የግብዕት እጥረት ለመቅረፍ ያስችላል ነው ያሉት።

በመሳፍንት እያዩ እና ቤዛዊት ተፈሪ

Exit mobile version