አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 16፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) እስራኤል በተመረጡ የኢራን ወታደራዊ ይዞታዎች ላይ ተደጋጋሚ የአየር ጥቃት መፈጸሟን አስታውቃለች።
የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ጥቃቱ ኢራን እና አጋሮቿ በእስራኤል ላይ ለፈጸሙት ተደጋጋሚ ጥቃት የተሰጠ አጸፋዊ ምላሽ ነው ብሏል።
ከሌሊት ጀምሮ በተፈጸመው ጥቃት በመዲናዋ ኢራን ምዕራብና ደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ የሚገኙ ወታደራዊ ተቋማት የጥቃቱ ኢላማዎች እንደነበሩ ተመላክቷል።
ጥቃቱን የፈጸሙት የእስራኤል ጦር አውሮፕላኖችም ኢላማቸውን መትተው በሰላም መመለሳቸው ነው የተገለጸው።
የእስራኤል መከላከያ ሃይል ቃል አቀባይ ሪር አድሚራል ዳኒየል ሃጋሪ በሰጡት መግለጫ፤ እስራኤል የተመረጡ የኢራን ወታደራዊ ዒላማዎች ላይ ጥቃት መፈጸሟን ተናግረዋል።
ኢራን ጥቃቱ መፈፀሙን ያረጋገጠች ሲሆን ጥቃቱን ተከትሎ ሁሉንም የአየር ክልሏን ዝግ ማድረጓን አስታውቃለች።
አሜሪካ እስራኤል በኢራን ወታደራዊ ይዞታዎች ላይ ስላደረሰችው ጥቃት መረጃው እንደነበራት ብትገልጽም፤ በጥቃቱ እጇን እንዳላስገባች መግለጿን ቢቢሲ ዘግቧል።