አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 15፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ወባ በፕላዝሞዲየም ጥገኛ ተውሳኮች የሚመጣ አጣዳፊ የትኩሳት በሽታ ነው።
የበሽታው ምልክቶች ከባድ ትኩሳት፣ ላብ፣ የሚያንዘፈዝፍ ብርድ ብርድ የሚል ስሜት፣ ራስ ምታት፣ የጡንቻ መጓጎል፣ ድካም፣ ማቅለሽለሽ፣ ማስመለስ፣ ተቅማጥና ትኩሳት፣ ብዙውን ጊዜ 38°C በላይ የሙቀት መጠን እና የጉበት እብጠት ናቸው፡፡
መተላለፊያ መንገዶቹ ምንድናቸው?
የወባ ተሕዋስያን፣ ፕላዝሞዲያ ተብለው የሚጠሩ ባለ አንድ ሴል ፍጥረታት ሲሆኑ ወደ ሰው ደም ውስጥ የሚገቡት አኖፊስ በምትባለው ሴት ትንኝ ንክሻ አማካኝነት ነው።
ተሕዋስያኑ የግለሰቡ ጥብቅ ሴሎች ውስጥ በመግባት ይራባሉ፤ በጉበት ውስጥ ያሉት ሴሎች ሲፈነዱ ተሕዋስያኑ ይወጡና የግለሰቡን ቀይ የደም ሴሎች ይወርራሉ።
ከዚያም ተሕዋስያኑ በቀይ የደም ሴሎቹ ውስጥ መባዛታቸውን እንደሚቀጥሉ የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
የወባ ተሕዋስያን ቀይ የደም ሴሎችን ይወርሩና ሴሎቹ እንዲፈነዱ ያደርጋሉ፤ ቀይ የደም ሴሎቹ በሚፈነዱበት ጊዜ ተሕዋስያኑ ይወጡና ሌሎች ቀይ የደም ሴሎችን ይወርራሉ።
በቀይ የደም ሴሎቹ ውስጥ የሚካሄደው ይህ ዑደት ይቀጥላል፤ ቀይ የደም ሴሎቹ በፈነዱ ቁጥር በበሽታው የተያዘው ሰው የወባ በሽታ ምልክቶች ይታዩበታል።
መከላከያ መንገዶች:-
ወባ በተደጋጋሚ በሚከሰትበት አካባቢ ለሚኖር ማህበረሰብ በፀረ ትንኝ ኬሚካል አብሮ የተሸመነ አጎበር በአግባቡ መጠቀም፣ የሚቻል ከሆነ በበር እና በመስኮቶቹ ላይ እንደ ወንፊት ያለ መከለከያ ማድረግ፣ እንደ አየር ማቀዝቀዣ ያሉ መሣሪያዎችን መጠቀም፤ ለትንኝ መራቢያነት አመቺ የሆኑ ውሃ ካቆሩ ቦታዎች ካሉ መራቅ እና ማጥፋት ናቸው፡፡
እንዲሁም በወባ የተያዘ ሰው በአፋጣኝ የሕክምና እርዳታ ለማግኘት ጥረት ማድረግ፣ ወባ በተደጋጋሚ ወደ ሚከሰትበት ቦታ ለመሄድ ጉዞ ከመጀመር በፊት ወቅታዊ መረጃ ለማግኘት መሞከር ጠቃሚ ነው፡፡
በወባ በሽታ የተያዘ ሰው በአፋጣኝ የሕክምና እርዳታ ለማግኘት ወደ ህክምና መሄድ ይኖርበታል። ነገር ግን በቸልተኝነት ወባ እስከ ሞት ሊዳርግ ይችላል።
በህክምና ማእከል ውስጥም በጤና ባለሙያ እንደ በሽታው ክብደት እና ቅለት አስፈላጊው ሕክምና ይሰጣል፡፡
በህክምና ማእከል ውስጥም የጤና ባለሙያዉ እንደ በሽታው ክብደት እና ቅለት አስፈላጊውን ሕክምና በአፍ በሚዋጥ ወይም በደም ስር በሚሰጥ መድሃኒት ህክምናውን የሚሰጥ ሲሆን÷ ከዚህ በተጨማሪ አጋዥ መድሃኒቶች እንደ ሙቀት መቀነሻ እና ህመም ማስታገሻ መድሃኒቶች የሚሰጥ ይሆናል።
ከዚም አልፎ ከወባ በሽታ ጋር ተያይዘው ለሚፈጠሩ ችግሮች እንደ ችግሩ መጠን አስፈላጊ እና ተመጣጣኝ ህክምና ይደረጋል።