አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 15፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የማሌዥያ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች በመሳተፍ ኢንቨስት ማድረግ እንደሚፈልጉ አስታወቁ፡፡
ወደ ማሌዥያ ለሥራ ጉብኝት ያቀናው የኢትዮጵያ ልዑክ በሀገሪቱ ከሚገኙ የቢዝነስ ማሕበረሰብ አባላት ጋር መክሯል፡፡
በዚሁ ወቅትም በኢትዮጵያ ስለሚገኙ ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጮችን የልዑካን ቡድኑ አባላት አብራርተዋል፡፡
በተለይም በማኑፋክቸሪንግ፣ በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ በፋርማሲዩቲካል፣ በቴክስታይልና ጋርመንት፣ በማዕድንና ኮንስትራክሽን ዘርፎች ላይ የማሌዥያ ባለሃብቶ እንዲሠማሩ ጥሪ ቀርቧል፡፡
ሀገራቱ መካከል ጠንካራ የኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲኖር፣ ኢትዮጵያ ስላላት የኢንቨስትመንት እድልና ቅድሚያ ስለሚሰጣቸው ዘርፎች እና ለባለሀብቶች ምቹ የኢንቨስትመንት ምኅዳር ለመፍጠር የተከናወኑ የሪፎርም ተግባራት ገለፃ ተደርጓል፡፡
የማሌዥያ ቢዝነስ ማሕበረሰብ አባላት በበኩላቸው÷ በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ የቅድመ ኢንቨስትመንት ጉብኝት የሚያደርግ ልዑክ እንልካለን ማለታቸውን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን መረጃ አመላክቷል፡፡
በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የኢንቨስትመንት ልውውጥም ለማሳደግ እንደሚሠሩ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል።