አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 15፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በ16ኛው የብሪክስ መሪዎች ጉባዔ ኢትዮጵያ ያነሳቻቸው አብዛኞቹ ጉዳዮች ተቀባይነት ያገኙ ነበሩ ሲሉ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ተናገሩ፡፡
በሩሲያ ካዛን የብሪክስ ጉባዔ የተወያየባቸው ጉዳዮች አስመልክቶ አምባሳደር ሬድዋን በሰጡት ማብራሪያ÷ በመድረኩ ሰፋ ያሉ ጉዳዮች መነሳታቸውንና ከዚህ ውስጥ በዓለም የተለያዩ ቀጣናዎች ብዙ ግጭቶች በመኖራቸው በርካታ ሰዎች እየተጎዱ ስለመሆኑ መነሳቱን ተናግረዋል፡፡
እንዲሁም አሁን ካለው የዲጂታል ዓለም ጋር ተያይዞ ከዳታ ስርቆት፣ የሀሰተኛ መረጃና የጥላቻ ንግግሮች መሰራጨት ጋር ተያይዞ ለዓለም ሰላም የራሱ ችግር እንዳለው መገለፁን ጠቅሰዋል፡፡
በተጨማሪ የፀጥታ ተቋማትን ከማሻሻል ጋር ተያይዞ፤ የብሪክስ አባል ሀገራት በራሳቸው ውስጥ ያለውን ልዩነቶች በማጥበብ የብሪክስን ውህደትና ጥንካሬ ለማምጣት የሚያስችሉ መግባባቶችን ማጎልበት እንደሚገባ፤ ልዩነቶች ካሉም እነሱን መፍታት እንደሚያስፈልግ እንዲሁም የብሪክስ አባል ሀገራትን የሚያቀራርቡ ስራዎችን መስራት የሚሉ መነሳታቸውን ገልፀዋል፡፡
በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ የራሷን ጉልህ ድርሻ በተለይም ካለችበት ቀጣና እና አህጉር ጋር ተያይዞ የጎላ ድርሻ መጫወት የምትችልበት ሰፊ ዕድል እንዳለ ለማየት መቻሉንም አምባሳደር ሬድዋን ተናግረዋል፡፡
ከጉባዔው ጎን ለጎን ከተለያዩ ሀገራት ጋር በተካሄዱ የሁለትዮሽ ውይይቶች ላይ ኢትዮጵያ እያደገች መሆኗ እና ካለችበት ቀጣና አንጻር የጎላ ሚና እንድትጫወት ብዙ ሀገራት አብረዋት የመስራት ፍላጎት እንደላቸው ማንሳታቸውን አመልክተዋል፡፡
በብሪክስ ስብሰባ ብዙ መድረኮች እንደነበሩ ያወሱት ዳይሬክተር ጀነራሉ፤ በመድረኮቹ ኢትዮጵያ ያስተላለፈቻቸው መልዕክቶች በአብኛው ተቀባይነት የነበራቸው እንዲሁም አጀንዳዎቹ በመድረኩ ተገቢነት ነበራቸው ነበሩ ብለዋል፡፡
በተጨማሪም በመድረኩ በሌሎችም ሴክተሮች ሌሎች የሁለትዮሽ ግንኙነቶችን የሚያጠናክሩ እድሎች መፈጠራቸውንና እነዚህ ውይቶችም እጅግ ውጤታማ መሆናቸውን ነው አምባሳደር ሬድዋን ያነሱት፡፡
በፌቨን ቢሻው