የሀገር ውስጥ ዜና

የብሪክስ አዲስ ልማት ባንክ ለኢትዮጵያ ትልቅ የፋይናንስ ዕድል የሚፈጥር ነው – ሀብታሙ ተገኝ (ኢ/ር)

By Mikias Ayele

October 25, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 15፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የብሪክስ አዲስ ልማት ባንክ ለኢትዮጵያ ትልቅ የፋይናንስ ዕድል የሚፈጥር ነው ሲሉ የማዕድን ሚኒስትር ሀብታሙ ተገኝ (ኢ/ር) ገለፁ፡፡

በሩሲያ ካዛን ከተማ በተካሄደው 16ኛው የብሪክስ ጉባኤ የኢትዮጵያ ልዑክ ያደረገው ቆይታ አስመልክቶ ማብራሪያ የሰጡት ሀብታሙ ተገኝ (ኢ/ር)፤ ብሪክስ በህዝብ ብዛቱ እና የኢኮኖሚ አቅሙ በዓለም ተፅዕኖ የሚፈጥር ስብስብ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ከዚህ አንፃር ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆኗ ትልቅ ትርጉም እዳለው ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ ከሌሎች የብሪክስ አባል ሀገራት ጋር በተለያዩ መስኮች በትብብር እየሰራች እንደምትገኝ ገልጸዋል።

በጉባኤው የመሰረተ ልማቶችን በፋይናንስ የሚያሳልጠው የብሪክስ አዲስ ልማት ባንክ ለኢትዮጵያ ትልቅ የፋይናንስ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

ልዑኩ በካዛን በነበረው ቆይታ በሩሲያ ከሚገኙ የተለያዩ የቢዝነስ ተቋማት ጋር ውይይት ማድረጉን ጠቅሰው፤ በውይይቱም የሩሲያ የቢዝነስ ተቋማት በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት ማሳየታቸውን ገልፀዋል፡፡

በተጨማሪም በጉባኤው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ በብሪክስ ያላትን አቋም ያስረዱበት እና ከተለያዩ መሪዎች ጋር የጎንዮሽ ውይይት ያደረጉበት እንደነበር ተናግረዋል፡፡