Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ኢትዮጵያን ለማሻገር የደም ዋጋ ተከፍሏል- ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 15፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያን ከእነ ሙሉ ክብሯ ለትውልድ ለማሻገር ባለፉት ዓመታት የደም ዋጋ ተከፍሏል ሲሉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ፡፡

117ኛው የመከላከያ ሠራዊት ቀን ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴን ጨምሮ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እና ከፍተኛ የመንግሥትና የሠራዊቱ አመራሮች በተገኙበት ተከብሯል፡፡

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ በዚሁ ወቅት እንዳሉት÷ ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማሻገር የደም ዋጋ ተከፍሏል።

በሠራዊት ግንባታ ኢትዮጵያ ቀዳሚ ከሆኑ ሀገራት መካከል መሆኗን ጠቅሰው÷ በአካባቢው ባላት ስልታዊ ጠቀሜታ ጠላትን ለመመከት የሚችል ሠራት እንዳላት አረጋግጠዋል፡፡

የውጭ እና ታሪካዊ ጠላቶች ኢትዮጵያን ለማዳከም በውስጣችን ጥላቻን ዘርተዋል ያሉት ፊልድ ማርሻሉ÷ የሀገራችንን ሠላም ለመንጠቅ እየሠሩ ነው ብለዋል፡፡

ጠላቶቻችን ራሱን በራሱ የሚያጠፋ ሀገር እንዲኖረን ቢሠሩም፤ በእኛ በኩል እየተከናወኑ ባሉ ሥራዎቻችን ደግሞ ጠላቶቻችን የበለጠ ተጨንቀዋል ነው ያሉት፡፡

ይህንን ለመመከትም የመከላከያ ሠራዊታችን ሕይወቱን ከፍሎ ሠላምን እና ልማትን ለማረጋገጥ ዋስትና ሆኗል ነው ያሉት፡፡

ታላቁ ህዳሴ ግድብን ለፍሬ ለማብቃት ሠራዊቱ እስከመጨረሻው እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸው÷ ሕዝብን መነሻ በማድረግ ለሥልጣን ከውጭ ኃይሎች ጋር የሚሠሩ አካላትንም አይቀጡ ቅጣት እየቀጣ ነው ብለዋል።

አሁን ላይ ሠራዊቱ በየአቅጣጫው አስቻይ አቅምን ገንብቷል፤ በሰው ኃይልም ይሁን በቴክኖሎጅ ሁሉንም ያሟላ የቀጣናው አስፈሪ ኃይል መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በጦርነት እየተፈተነ በእሳት ውስጥ ሆኖ የወጣ ሠራዊት ባለቤት ሆናለች ያሉት ፊልድ ማርሻሉ÷ በዚህ ግንባታ ውስጥ ደግሞ ኃላፊነታቸውን ለተወጡ ሁሉ ምሥጋና ይገባል ነው ያሉት፡፡

በዓለምሰገድ አሳዬ እና ሶሎሞን ይታየው

 

Exit mobile version